3ኛው ዙር የ'8100A' አጭር የጽሁፍ መልዕክት ዕጣ አሸናፊ ሽልማቱን ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
3ኛው ዙር የ'8100A' አጭር የጽሁፍ መልዕክት ዕጣ አሸናፊ ሽልማቱን ተረከበ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማሰባሰቢያ የ”8100A” አጭር የጽሁፍ መልዕክት 3ኛ ዙር ሽልማት የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር "ሀይሉክስ" ተሽከርካሪ ለአሸናፊው ተበረከተ።
የ"8100A" 3ኛ ዙር ሽልማት ሥነ-ስርዓት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ተከናውኗል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ እና ተሽከርካሪውን ለግድቡ ያበረከተው ሞኤንኮ ኩባንያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የ3ኛ ዙር ባለዕድለኛ በደቡብ ክልል ኮንታ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብርሐም አለሾ ከአቶ መላኩ አለበል የተሽከርካሪውን ቁልፍ ተረክበዋል።
አቶ መላኩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት መሆኑን ገልጸው፤ የግድቡ ስኬታማነት የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
''ግድቡ የሚገነባው የራሳችንን ሳናጎድል ለሌሎች መትረፍ እንደምንችል በተግባር የምናሳይበት የኢትዮጵያዊነት ነጸብራቅ ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሃይል ለአንድ አገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
''የራስን ያልሆነ ነገር ያለመመኘትና የራስን አሳልፎ ያለመስጠት የኢትዮጵያዊነት ባህላችን በህዳሴ ግድብ ጎልቶ የሚታይ እውነታ ነው'' ብለዋል።
አክለውም ወቅቱ ለግድቡ ያለንን ድጋፍ በማጠናከር ፍጻሜውን የምናበስርበት እንጂ የምናስተጓጉልበት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ፤ ግድቡ ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ቁጠባን የሚያሳድግበት እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የግድቡ መጠናቀቅን ተከትሎ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ከዚህ በፊት የሞኤንኮ ኩባንያ ለ8100A አጭር የጽሁፍ መልዕክት አሸናፊዎች ተመሳሳይ ተሽከርካሪዎችን ሲያበረክት ቆይቷል።
ኩባንያው ግድቡ ሲጀመር የ20 ሚሊዮን ቦንድ መግዛቱን እና ወደፊትም በድጋፍ አጋርነቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል።