በኢትዮጵያ ተጨማሪ 250 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ8 ሰዎች ሕይወት አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 250 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ8 ሰዎች ሕይወት አልፏል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 5 ሺህ 414 የላቦራቶሪ ምርመራ 250 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ። 144 ሰዎች ደግሞ በትናንትናው ዕለት አገግመዋል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ ዛሬ ባወጡት መግለጫ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 425 ደርሷል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 240 ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አስር ደግሞ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው። ከነዚህም 158 ወንዶችና 92 ሴቶች ናቸው።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከሶስት ወር እስከ 90 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ መግለጫውያመለክታል።
ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 177 ከአዲስ አበባ፣ 21 ከትግራይ፣ 20 ከአማራ፣ 18 ከጋምቤላ ክልል፣ 8 ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 1 ሰው ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና 1 ሰው ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ናቸው።
በተጨማሪም በአስክሬን ምርመራ 6 ሰዎችና በሕክምና ማዕከል ውስጥ ሕክምና ሲደረግላቸው የነበሩ 2 ሰዎች በአጠቃላይ የ 8 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በዚህም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 89 ደርሷል። 27 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕክምና ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል።
በትናንትናው ዕለት 144 ሰዎች በማገገማቸው በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 688 ደርሷል።
በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች 3 ሺህ 646 ናቸው።
በኢትዮጵያ እስካሁን 237 ሺህ 464 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።