ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለ45 ተከታታይ ቀናት ለ1 ሺህ 500 ሰዎች የምሳ ምገባ ያካሂዳል

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2012(ኢዜአ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለ45 ተከታታይ ቀናት ለ1 ሺህ 500 ሰዎች የምሳ ምገባ መርሃ ግብር ያካሂዳል። 

ማህበሩ መርሃ ግብሩን የሚያካሂደው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ላደረጉ ሰዎች ሲሆን፤ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ያስከተለውን ጫና መሰረት በማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር  ከኮካ ኮላ  ፋዉንዴሽን  እና  ከሰብአዊ  ድጋፍ  ጥምረት  ጋር  በመተባበር ድጋፉን እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ዶክተር መሸሻ  ሸዋረጋ እንደገለጹት፤ ድጋፉ የተደረገዉ  ወረርሽኙ ያስከተለውን ጫና ለመቋቋም በማሰብ ነው።

ማህበሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያየ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ዶክተር መሸሻ ተናግረዋል።

በተለይም መንግሥት ለጤና መዋቅሩ ያዘጋጃቸዉ የማቆያና  የማከሚያ ቦታዎች ላይ  ምግብ ነክ ያልሆኑ ለበሽታው መከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

በጎዳና ላይ ለሚኖሩ  ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን በማዘጋጀት ድጋፍ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ዛሬ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም በዘላቂነት እንዲተገበር እድሮች ዋነኛ መንገዶች በመሆናቸዉ ስልታዊ  የሆነ ትስስር  እና  ህብረት በመፍጠር ተቀናጅቶ  መሥራት  እንደሚያስፈልግ  ጠቁመዋል፡፡

የኮካ ኮላ ፋውንዴሽን ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዲውል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም