የሕዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት ስራን በተያዘለት ጊዜ ለመከወን ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት ስራን በተያዘለት ጊዜ ለመከወን ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ስራ ለመከወን ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የሕዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ 9ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን ግንባታው 74 በመቶ ደርሷል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በራስ አቅምና በሕዝቦቿ ቁርጠኝነት አሁን ለደረሰበት ደረጃ አብቅታለች።
አሁን ግድቡን ውሃ ለመሙላትና በዓባይ ወንዝ ለመጠቀም የሚያስችላት አቅም ላይም ደርሳለች።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ግድቡ ውሃ ለመያዝ የሚችልበት ከፍታ ላይ እየደረሰ መሆኑንና የውሃ ሙሌት ስራ ለማከናወንም ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ገልጿል።
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግድቡ ቅድሚያ ኃይል የሚያመነጩት ሁለት ዩኒቶች ያሉበት አካባቢ የብረታ ብረት ስራዎችን የማጠናቀቅ ስራ እየተሰራ ነው።
የኤሌክትሮ መካኒካል ጄኔሬተር ተከላ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በየቀኑም 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ሲሚንቶ እየተሞላ ነው።
ግድቡ ውሃ ለመያዝ የሚያስችለው ከፍታ ላይ ለመድረስ እስካሁን 35 ሜትር የተጠናቀቀ ሲሆን 3 ሜትር የሚሆን ብቻ እንደሚቀረው ተናግረዋል።
የውሃ ማስተላለፊያ የብረት አሸንዳዎች ስራ ተጠናቋል፤ የታችኛው ውሃ ማስወጫ በር ገጠማ ስራ እየተከናወነና የብረታ ብረት ስራዎቹ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄዱ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ ዘንድሮ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይሞላል፤ በዚህም መጀመሪያ ኃይል የሚያመነጩት ሁለቱ ዩኒቶች ኃይል መስጠት የሚጀምሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ነው ያሉት።
የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለግድቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ እንደቀጠለ ነው የገለጹት።
ባለፉት 11 ወራት ከ657 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በመጥቀስ።
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝና የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያላትን መብትና አቋም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ስራዎች እየተሰሩም ይገኛሉ።
በተለይም የተፋሰሱ አገራት አብዛኞቹ የዓረብኛ ቋንቋ ተጠቃሚ ከመሆናቸው አኳያ ቋንቋውን የሚናገሩ ዜጎችን በማሰባሰብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ የማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን በበለጠ እንዲያጠናክር ጥሪ ቀርቧል።
ግድቡ በመጪው ሐምሌ ውሃ ለመሙላት የተያዘውን እቅድ እንዲሳካ ከወዲሁ የደን ምንጣሮ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ 2 ሺህ አባላትን የያዙ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራው መግባታቸውን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታሉ።