ቀጥታ፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ በድጋፍ አገኘ

ነቀምቴ ሰኔ 19/2012(ኢዜአ) በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ተወላጆች የተቋቋመውና 'ሶሳይቲ ፎር ኤዱኬሽን ኢንቫይሮሜንት ደቨሎፕሜንት' የተባለው ድርጅት ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ከድጋፉ መካከል  የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ የፊትና አፍ መሸፈኛ ጭንብል ፣  የጤና ባለሙያዎች አልባሳትና  ኮምፒተሮች ይገኙበታል።

ከተወላጆቹ መካከል  የግብርና ሚኒስትር  ዴኤታ ዶክተር ከባ ኡርጌሣ ከበሽታው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአካባቢው ህብረተሰብ  እንዳይጎዳ ለማገዝ  ተወላጆች በመተባበር  ያመቻቹትን ድጋፍ   ለዞኑ አስተዳደር ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል እንዲያግዝ ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪም ለሁለት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ለወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ  መጻሕፍት  መለገሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ ተወላጆች በመተባበር ከድርጅቱ ጋር በመሆን  ያደረጉት ድጋፍ  የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ናቸው፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፉፋ በበኩላቸው የድርጅቱ አባላትና  ሌሎች የአካባቢው  ተወላጆች በመተባበር የዞኑን ህብረተሰብ ከበሽታ ለመታደግ ያደረጉት  ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ከግንዛቤ ጉድለት በበሽታው እንዳይጠቃ ተተከታታይነት ያለው ግንዝቤ መፍጠር ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የዞኑ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነገራ ፈይሣ ድጋፉን ላደረጉት አካላት አመስግነዋል።

ድጋፉንም ለጉዱሩና አቤ ደንጎሮ ሆስፒታሎች እንዲሁም  ለሚያስፈልጋቸው ሌሎች የጤና ተቋማት እንደሚከፋፈም አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ዊርቱ  ተወላጆቹ  የወጠበትን ህዝባቸውን ማስታወሳቸው  በማመስገን ለወደፊቱም ሁሉም በመተባበር ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም