ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን መከላከል ልምዷን ለዓለም የጤና ድርጅት አባል አገሮች አካፈለች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ/18/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ያከናወናችውን ተግባራትና ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች ለዓለም የጤና ድርጅት አባል አገሮች አካፈለች።

ኢትዮጵያ ልምዷን ያካፈለችው ዛሬ የዓለም የጤና ድርጅት ጉባዔ ከአባል አገሮች ጋር ባካሄደው ጉባዔ ነው።

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በመታገዝ በተከናወነው ጉባዔ ወረርሽኙን የተከላከለችው ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ሳታደርግና የቫይረሱ ስርጭት የከፋ ጉዳት መከላከሏን ለተሳታፈዎቹ አስረድታለች።

በጉበዔው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ ከ194 አገሮች የተወጣጡ የጤና ሚኒስትሮች ተሳትፈውበታል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህን ወቅት ኢትዮጵያ ድርጅቱ በሽታውን ዓለም አቀፍ ስጋት ብሎ ከማወጁ ቀደም ብላ የጥንቃቄ ስራዎችን መጀመሯን ተናግረዋል።

አገሪቷ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ መንገደኞች መተላለፊያ ማዕከል አንደመሆኗ መጠን ጥብቅ የመግቢያና መውጫ ልየታ መጀመሯንም ለአብነት አንስተዋል።

የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮም የለይቶ ማቆያዎችንና የሕክምና መከታተያ ጣቢያዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።

ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላም ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና ከውጭ የሚመጡ ግለሰቦች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያዎች እንዲገቡ መወሰኑን ተናግረዋል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከሚያዝያ 8 ቀን2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታውጆ ሙሉ ለሙሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሳይገደብ የጥንቃቄ አቅጣጫዎችን ተፈጻሚ መደረጋቸውንም አውስተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ምንም የምርመራ አቅም ካልነበረበት ሁኔታ አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጡ 38 የመመርመሪያ ጣቢያዎችን በአጭር ጊዜ ማቋቋም ተችሏል ብለዋል።

ሌሎች ተጨማሪ ላቦራቶሪዎችም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ዕለታዊ ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት ድረስ 227 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ምርመራ መደረጉንና ይህም ከአፍሪካ አራተኛ ደረጃ የሚይዝ የምርመራ አፈጻጸም መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ካለን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር አንጻር አሁንም በስፋት መስራት እንዳለብን እንገነዘባለን ብለዋል።

በርዕሰ መዲናዋ አዲስ የተገነባ ሆስፒታልና ትልቁን የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶላቸው ለቫይረሱ ምላሽ ስራ አንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሚመራው ጤና ምላሽ ሥራም 12 ከሚሆኑ የጤና ዘርፍ የሙያ ማህበራትና በውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አማካሪ ቡድንን ያሳተፈ ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል።

የግሉ ዘርፍም በሥራው እንዲሳተፍ ተደርጓልም ነው ያሉት ዶክተር ሊያ።

የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል በተጓዳኝ እንደ ህጻናትና እናቶች ጤና ያሉ መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት እንዳይቋረጡ ሰፊ ስራ መሰራታቸውንም ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የወባ፣ የቢጫ ወባ፣ የኩፍኝና ኮሌራ ወረርሽኞች ተከስተው እንደነበርና ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንደተቻለም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሟላ ግብዓት ያላቸው የለይቶ ማቆያዎች እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል።

የቫይረሱ መከላከያ ግብዓቶች እጥረትና በኢትዮጵያ የተጠለሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገሮች መኖራቸውም ኢትዮጵያ መሻገር ያለባት ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑንም ዶክተር ሊያ አስረድተዋል።

የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉት ያለውን ተጋድሎም ''እጅግ የሚያኮራ'' በማለት ለተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም