በኢጃጂ ከተማ ለአቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኢጃጂ ከተማ ለአቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
አምቦ፣ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢጃጂ ከተማ ለ500 አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የምግብ እህልና ንጽሕና መጠበቂያ ድጋፍ ተደረገ።
የኢሉ ገላን ወረዳ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ከበጎ ፍቃደኞች ያሰባሰበው ድጋፍ፤ 200 ኩንታል በቆሎና ስንዴ፣ 600 ሊትር ዘይት እንዲሁም የንጽሕና መጠበቂያ ሣሙና ነው።
ከ238 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ለእነዚሁ ወገኖች ዛሬ ተከፋፍሏል።
የወረዳው አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሐጽድቅ እንዳሉት ድጋፉ የተመቻቸው የኮሮና ቫይረስ ክስተት ተከትሎ እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝ ነው።
በቀጣይም ወረርሽኙ ከሀገሪቱ እስኪወገድ ድረስም በከተማዋ ውስጥ ለሚገኙ ችግረኞች የተጀመረውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢሉ ገላን ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ፈጠነ አጉማ በጎ ድጋፈን ለዳረጉት ወገኖች አመስግነዋል።
በበሽታው ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ ሌሎችም ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሒሩት በፍቃዱ በሰጡት አስተያየት በከተማ በየሰው ቤት እየዞሩ ልብስ አጥበው ይተዳደሩ እንደነበር ገልጸው፤ በበሽታው ምክንያት ሥራ በማጣት ለችግር በተጋለጡበት በዚህ ወቅት ባገኙት ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በተመሣሣይም የአምቦ ውኃ ፋብሪካ ለአምቦ ከተማ ችግረኞች 400 ሊትር ሳኒታይዘር መስጠቱን የከተማው አስተዳደር ከንቲባና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ሣህሉ ድርብሳ ተናግረዋል።
ድጋፉን ላደረገው ተቋምም ምሥጋና አቅርበዋል።