ማህበሩ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጥቅምና የሙያ ነጻነት ለማስከበር እሰራለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጥቅምና የሙያ ነጻነት ለማስከበር እሰራለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012(ኢዜአ) በዚህ ዓመት የተመሰረተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጥቅምና የሙያ ነጻነት መከበር እንደሚሰራ ገለጸ።
ማህበሩ አመሰራረቱንና ቀጣይ ሥራዎቹን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ መሠረት በዚሁ ወቅት ለባለሙያዎች መብትና ጥቅም መከበር ይሰራል።
ለጋዜጠኞች ጥብቅና በመቆም ሙያውን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ማህበሩ ከአራት ወራት በፊት መሥራች ጉባዔውን በማድረግ የማህበሩን አደረጃጀት በማጽደቅና ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች በመምረጥ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል።
ከሲቪክ ማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲም ሕጋዊ እውቅና እንዳገኘም አቶ ኤልያስ አስረድተዋል።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ በጋሻው በበኩላቸው ማህበሩ ባለሙያዎች በሥራቸው ምክንያት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ዘርፉን ሊያቀጭጩ የሚችሉ ሕጎች እንዳይወጡም ይታገላል ብለዋል።
በባለሙያዎች ላይ የተለያዩ አካላት ተጽእኖና ጫና ሲያደርጉ ድምፁን የሚያሰማ ማህበር ባለመኖሩ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን አቶ ኤርሚያስ አስታውሰዋል።
ማህበሩ 600 አባላት በማህበራዊ ትስስር ገጹ የመዘገበ ሲሆን፤የማህበሩን ደንብና መመሪያ ተቀብለው፣መዋጮ ለመክፈል ፈቃደኛ ባለሙያዎችን ይቀበላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አሥርታት ከአምስት ያላነሱ የጋዜጠኞች ማህበራት የተመሰረቱ ቢሆንም፤ለአባላት መብትና ጥቅም ያልቆሙ፤ለሙያው ዕድገትና ነፃነት እንዳልሰሩ የሙያው ባለቤቶች ይናገራሉ።
ማህበራቱ በአመራርነት የሚቀመጡ ሰዎች መጠቀሚያ በመሆን በስፖንሰርሺፕ የሚገኘውን ጥቅም ለግል ጥቅም በማዋልና ለውጭ ጉብኝት ሲጠቀሙባቸው ነበር።