የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በድሬዳዋ በኮቪድ-19 ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በድሬዳዋ በኮቪድ-19 ምክንያት ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
ድሬዳዋ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ 831 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የድሬዳዋ ቀይ መስቀል ማህበር ኃላፊ ወይዘሮ በሐር አደም እንደገለፁት ድጋፉ ለ500 ችግረኛ ወገኖች የተደረገ ሲሆን በነፍስ ወከፍ 10 ኪሎ ግራም ማካሮኒ ፣ 1ካርቶን ፓስታ ፣ 10 ኪሎ ግራም ዱቄትና 3 ሊትር ዘይት እንዲደርሳቸው የታሰበ ነው።
በተጨማሪም ለ500 አካል ጉዳተኞች የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር መሰጠቱን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ይህ ድጋፍ ከስዊዝ ቀይ መስቀል የተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በቅርቡም ከዩኒሴፍ በተለገሰ ገንዘብ በአንበጣ መንጋና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ድጋፉን ተቀብለው ለተረጂዎች የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት ኮሮና የሚያስከትለውን ችግር ተቋቁሞ ነገ የተሻለ ለማድረግ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የ75 ዓመት አዛውንት ወይዘሮ አሰኝ አበበ በሰጡት አስተያየት ምንም ረዳት እንደሌላቸውና በልመና እንደሚተዳደሩ ገልፀው ቫይረሱን ሽሽት ወደ ውጭ ስለማይወጡ የእለት ምግብ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
አሁን ለተደረገላቸው ድጋፍ የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የአክሱምና ዓድዋ ከተማ ነዋሪዎች የ263 ሺህ ብር ግምት ያለውን የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
በአክሱም ከተማ የዳያስፖራዎች ማህበር አስተባባሪ ተወካይ አቶ ናትናኤል ፍጹም እንዳሉት በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአክሱም ተወላጆች የላኩትን 210 ሺህ ብር በከተማ ለሚኖሩ 100 የተቸገሩ ዜጎች ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ በነብስ ወከፍ 50 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት፣አምስት ሊትር ዘይት እና አምስት ኪሎ ሽሮ ያካተተ ነው ብለዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን ለመከላከል እንዲረዳቸውም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
በአሜሪካ የሚኖሩ የአድዋ ከተማ ተወላጅ ወይዘሮ ኤልሳ እምባዬ በበኩላቸው ለ75 የተቸገሩ ወገኖች 63 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ለሚገኙ 650 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉን ያደረጉት አደምስ ተርማል ሲስተም ፋውንዴሽን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅትና ነጋዴዎች ናቸው።
አደምስ ተርማል ሲስተም ፋውንዴሽን የሆሳዕና ቅርንጫፍ አስተባባሪ ተወካይ አቶ አቡሬ ጎበና እንዳሉት ድርጅቱ ለ600 ወገኖች በነፍስ ወከፍ 24 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ 12 ኪሎ ግራም ሩዝና ማካሮኒ እንዲሁም ስድስት ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ አድርጓል።
በተመሳሳይ በከተማው የሚገኙ የታይዋን ነጋዴዎች ከ50 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ 50 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስተባባሪው አቶ ይድነቃቸው ሀንዲሶ ገልፀዋል።
በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል አባልና የሴቶች፡ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋጤ ጀማል እንደተናገሩት በወረርሽኙ ምክንያት ሰርተው መብላት ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም ወገን እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ መረጠች አዳነ ድጋፍ ያደረጉላቸው ወገኖችን አመስግነዋል።