ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድሮች የጋራ ተጠቃሚነትን መርኋን አንጸባርቃለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድሮች የጋራ ተጠቃሚነትን መርኋን አንጸባርቃለች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት መርኋን እንዳንጸባረቀች የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አስልጣኞችና የቀድሞ ተጫዋች ተናገሩ።
ሕዝቡ የግድቡን ግንባታ በጀመረው መልኩ እንዲያጠናቅቅም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞውና የአሁኑ ዋና አሰልጣኞችና የቀድሞው ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
"ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት የምታስብና በዙሪያዋ ያሉ ሀገራት በችግርና ድህነት ሲጎዱ ማየት ስለማትፈልግ በምድሯ የፈለቀውን የአባይ ወንዝን በጋራና በፍትሃዊነት እንጠቀም" ማለቷን የቀድሞው ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ተናግረዋል።
አገሪቱ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ስለምታምን ለዓመታት በዘለቁት ድርድሮች አቋሟን ሳትለዋውጥ መቆየቷን አስረድተዋል።
ነገር ግን ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ የፈለቀውን ወንዝ ለብቻችን እንጠቀም ማለታቸው ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።
ኢንስትራክተር ሰውነት "የኢትዮጵያ ሕዝብም የህዳሴው ግድብን በጋራ ሆኖ በመጨረስ ፍላጎቱን እውን ያደርጋል"ሲሉ ለልማት ያለውን ተነሳሽነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው "ሕዝቡ ከድርድሩ በስተጀርባ የህዳሴ ግድብን በመተባበርና በመደጋገፍ ጨርሶ ወደ ተሻለ ብልፅግና ይሻገራል" ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እያደረገ ያለው የዲፕሎማሲ አካሄድ አበረታታች ነው ብለዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የህዳሴ ግድቡ ነገን የተሻለ ለማድረግ በአስተዋፆው እየተገነባ ያለው ግድብ በመሆኑ ለድርድር እንደማይቀርብ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብድን ተጫዋች ደጉ ደበበ ተናግሯል።
መንግሥትም በግድቡ ድርድር እያሳየ ያለውን አቋም የሚደገፍና ''ኢትዮጵያዊ እሴት'' የያዘ ነው ብሎታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 74 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በቀጣዩ ወር ውኃ መያዝ ይጀምራል።
በቤንሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጉባ ወረዳ ሲርባ በተባለ ቦታ እየተገነባ ያለው ግድብ ሲጠናቀቅ 187 ሺህ 400 ሄክታር መሬት የሚሸፍን 246 ኪሜ ሰው ሰራሽ ውኃ ይፈጥራል።
ግድቡ 6ሺህ ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።