ቀጥታ፡

በሁመራ ከተማ የኮሮና ቫይረስ መመርመርያ ማእከል ስራ ጀመረ

ሁመራ፣  ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላቦራቶሪ ማእከል ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

በምረቃው ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጸጋይ በሪሁ እንደገለጹት የምርመራ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት መጀመር በዞኑ እየተስፋፋ የመጣውን ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው።

የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ችግር ለማቃለል በዞኑ የቤት ለቤት አሰሳ፣ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች እንዲሁም የመከላከልና የናሙና መውሰድ ተግባራትን ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል::

ቫይረሱ ወደ ዞኑ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚለዩ ሰዎችን ናሙና ወደ መቀሌ በመላክ ተጨማሪ ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል ይጠይቅ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ትናንት ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመመርመሪያ ማእከሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ እስከ 94 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

ማእከሉ ለጊዜው ስድስት የላብራቶሪ ባለሙያዎችን ይዞ ስራ የጀመረ ሲሆን ባለሙያዎቹ በሦስት ሽፍት ተመድበው  አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የላቦራቶሪው አገልግሎት መጀመር በተለይ በለይቶ ማቆያ ለሚገኙ ወገኖች ፈጣን የምርመራ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ጊዜያቸውን ጨርሰው ለሚወጡ ታካሚዎች ድጋሚ ተመርምረው ጤናቸውን ተረጋግጦ ከማእከሉ እንዲወጡ ያስችላል።

የመመርመርያ ላብራቶሪው አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተወልደ ውብአየሁ ናቸው።

በመሆኑም ከኮቪድ-19 በተጨማሪ ተያያዥነት ላላቸው በሽታዎች በቀጣይ በርካታ ምርምሮችን ለማካሄድ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

የማዕከሉ መገንባት በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የመመርመር አቅም የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቁመዋል::

በትግራይ ክልል ሁመራን ጨምሮ አራት መመርመርያ ማዕከላት እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።


የዞኑ አስተዳደር አቶ ርስቁ አለማው ላባራቶሪው በተመረቀበት ወቅት እንደገለጹት የዞኑ ኢንቨስትመንት በአግባቡ እንዳይተገበር እና ለህብረተሰቡ ጤና እንቅፋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመግታት ጤና ቢሮውና የሚመለከታቸው አካላት እያደረጉት ላለው ተግባር አመስግነዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም