ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በውይይት፣ በድርድርና በሃሳብ የበላይነት መፍታት ይገባል --- የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) አለመግባባቶችን በውይይት፣ በድርድርና በሃሳብ የበላይነት የመፍታት ልምድን ማዳበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለጸ።

የመገዳደል ውጤት ድህነትን ማስከተል፣ ቁርሾን ጥሎ ማለፍ እና የታሪክ ተወቃሽ ማድረግ መሆኑንም ማህበሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ከመገዳደል አስተሳሰብ በመውጣት አለመግባባቶችን በድርድር፣ በሃሳብ የበላይነትና በመቻቻል መፍታት ይገባልም ብሏል።

ከሰሞኑ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማስፈን የጀመሩትን ጥረት እንደሚደግፍና የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥላቻ የጸዳ ውይይት በማድረግ የጋራ አገራዊ ጥቅምና ህልውና በማስቀደም ለሰላም የበኩላቸውን እንዲያበረክቱም ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል።

ከሰላም እጦት በተጨማሪ በውጭ ሃይሎች ጫና ለመፍጠር እየተሞከረ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልል የመምህራን ማህበራትም ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተሉና ድርሻቸውን ወጥተው እንዲያስተባብሩም አሳስቧል።

ኢትዮጵያ ከቀድሞ ታሪኳ ጀምሮ ዜጎቿ ከእርስ በርስ ጦርነት ተለይተው በሰላም የሚኖሩበት ጊዜ ውስን ቢሆንም የውጭ ወረራ ሃይል ባጋጠመ ጊዜ ግን ሁሉም በጋራ በመቆም አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በ1941 ዓ.ም የተመሰረተ እና በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺህ በላይ አባላት አሉት።

በአሁኑ ወቅትም አፍሪካን በመወከል ትምህርት አለም አቀፍ የተባለ አለም አቀፍ መምህራን ማህበር ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም