ቀጥታ፡

መንግሥት በወረርሽኙ ምክንያት የተዳከመውን ኢንቨስትመንት ለመደገፍ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012(ኢዜአ) መንግሥት በኮቪድ-19 ምክንያት እየተዳከመ የመጣውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመደገፍና ከውድቀት ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽሕፈት ቤቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢንቨስትመንቱ ላይ ያሳደረውን ተፅኖና የመንግሥትን ምላሽ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአማካኝ ከ50 በመቶ በማደግ ላይ የነበረ ሲሆን፤ በ2010 ዓ.ም ወደ 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሎ እንደነበረም አስታውሷል።

በዚህም ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት፤ ከአፍሪካ ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንዳስቻላት የጠቆመው መግለጫው፤ ይሄንንም ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግሥት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የንግድ ከባቢውን በማስተካከል ተከታታይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አመልክቷል።

በዚህ ጠንካራ የእድገት ማሻሻያ ሥራ ታግዞ በያዝነው ዓመት የሀገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያድጋል ተብሎ ቢገመትም ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት የተስተጓጎለው የዓለም የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ ተከትሎ ፍሰቱ ከሚጠበቀው በታች ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽ/ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል።

በተለያዩ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ትንተና በ2012/13 ዓ.ም ዓለም አቀፉ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከ30 እስከ 40 ከመቶ እንደሚቀንስ ግምት ማስቀመጡን ያመለከተው መግለጫው፤ ይህ ተፅኖም በሀገራችን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቅሷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደየ ዘርፉ የሚለያይ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ በአጠቃላይ ወረርሽኙ የሚያሳድረውን ጫና በፍላጎት፣ በአቅርቦትና በፋይናንስ ዘዴዎች ከፋፍሎ ማየት እንደሚቻል አስረድቷል ጽ/ቤቱ።

ምንም እንኳን የፍላጎትና አቅርቦት ጫና እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አለመረጋጋት ቢኖርም እስከ አሁን በታየው ሂደት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት ማሳየት መቀጠላቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ከመድኃኒት ምርቶችና ከግብርና ጋር የተዛመዱ ፍላጎቶች አሁንም ከፍተኛ ናቸው ያለው መግለጫው፤ ከፍተኛ ፍላጎት የታየባቸው እንደ ቂሊንጦ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ፓርክና የአግሮ ኢንዲስሪ ፓርኮች ያሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተጠቅሷል።

በተቃራኒው የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ከፍተኛ የፍላጎት አለመረጋጋትና የእሴት ሰንሰለት መረበሽ ምክንያት አዳዲስ ኢንቨስትመንት የመሳብ እድሉ አነስተኛ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ የውጭ ንግድ ተኮር ከሆኑት ዘርፎች መካከል የሆቴል ኢንዱስትሪው ክፉኛ መጎዳቱን አስታውሶ፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሆቴሎች ከ80 ከመቶ በላዩ ሥራ ማቆማቸውን አመልክቷል።

በዚህም ዘርፍ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች ይመጣል ተብሎ እንደማይታሰብም መግለጫው አመልክቷል።

ከዚህ በፊት ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለው ሌላው የውጭ ንግድ ተኮር ኢንዱስትሪ የአበባ ምርት ነበር ያለው መግለጫው፤ የወረርሽኙ ጫና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአበባ ፍላጎት ተጽዕኖ ማሳደሩን አመልክቷል።

በዚህም የሀገራችን የአበባ አምራቾች እንቅስቃሴ መስተጓጎል በሥራ፣ በሠራተኞች ገቢ እና ተጨማሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ ዕድሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን መግለጫው አስታውሷል።

እነዚህንና ሌሎች ወረርሽኙ በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም መንግሥት ባለሀብቱን በተለያየ ሁኔታ የመደገፍና የማበረታታት ሥራ እያከናወነ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም መንግሥት ባለሀብቱ ተጽዕኖውን እንዲቋቋሙ በፋይናስና በተግባር መደገፉን ያመለከተው መግለጫው፤የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የሚውል 15 ቢሊዮን ብር ይፋ ማደረጉን አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስተዋፆ ለሚያበረክቱ ባለሀብቶችም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ባንኩ እያመቻቸ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

በትግበራ ድጋፍም አስመጪና ላኪ ባለሀብቶችን ለማገዝ በሎጀስቲክ ዘርፍ የተለያዩ የሀገር ውስጥ የታሪፍ ማሻሻያና ቅናሽ መደረጉን ያመለከተው መግለጫው፤ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የማምረቻ ዕቃዎችን ከሞጆ ወደ ጅቡቲ በነፃ እንዲያመላለስ መደረጉንም አስታውቋል።

የወደብ ክፍያዎችም ለጊዜው እንዲቀሩ መደረጉንምን፣ እንዲሁም የንግድ ምዝገባና የኢምግሬሽን አገልግሎቶች እንዲቀነሱ መደረጉንም መግለጫው አመልክቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውሉ ዕቃዎችን ለማምረት ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት ያለው ቀረጥ እንዲቀር መደረጉን ያመለከተው መግለጫው፤በአትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ላይ በብሔራዊ ባንክ የተጣለው ዝቅተኛ ዋጋ እንዲነሳ መደረጉም ተመልክቷል።

መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጫናን በቅርበት እያጠናና እየተከታተለ ለድህረ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መልሶ ቢያገግም እንኳን አስፈላጊ የፖሊሲ እርምጃዎች በመለየት ላይ እንደሚገኝ መግለጫው አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም