ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ስምምነቶችን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን ሹመት ጨምሮ የተለያዩ ስምምነቶችን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

በዚህም የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ሹመት እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለመመደብ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አፅድቋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅም አፅድቋል።

የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም በምክር ቤቱ ፀድቋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኳታር መንግስት የማዕድን ሥራዎች አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅም ፀድቋል።

በኢትዮጵያና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለበረሃ አንበጣ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅም  እንዲሁ።

ኢትዮጵያ እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ እንዲያግዝ ለሁለተኛው የኢትዮጵያ የእድገትና ተወዳዳሪነት የልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነትም ፀድቋል።

በምክር ቤቱ የዛሬው ውሎ በኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነትም መፅደቁ ታውቋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ እና በሩዋንዳ መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነትም አፅድቋል።

በሁለቱ አገራት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት የሚያስችለው ስምምነትም ፀድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም