የመቶ ቀናት ጀምበር በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር

104
አየለ ያረጋል (ኢዜአ) በርግጥ የካፌው መድመቂያ ሰዓት ነው። እናም ደምቋል። የዛሬው ከምንግዜውም ይለያል፡፡ ልክ ሰባት ሰዓት ፒያሳ የሚገኘው ካፌ በሰው ‘ጎርፍ' ተጥለቅልቋል፤ ከአፍ እስከ ገደፉ። ደንበኛ፣ አስተናጋጅ፣ ባሬስታ፣ ምግብ ሰሪ... ሁሉም አንድ ቦታ ላይ አፍጥጧል፤ ከምስለ መስኮቱ /ቴሌቪዥኑ/። የእኔ ዐይኖችም ሁለት ነገሮች ላይ ይፈራረቃሉ - ከካፌው ድባቡና ከምስለ መስኮቱ..... ምናልባትም ይቺን ቅጽበት ብዙኃኑ በ"ብርሃን ፍጥነት እንዲህ ይሆናል" ብሎ ፈጽሞ አልጠበቀ ይሆናል። ግን ሆነ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) 55 ደቂቃዎች በረሩ። 'ሺ ሰማንያ' ኪሎ ሜትሮችን በኢትዮጵያ ጢያራ ከንፈው ሰሜናዊት ኮከብ ላይ ከተሙ። በዕድሜ እኩዮችን አዲስ አበባና አስመራን ከ20 ዓመታት በፍቅር ናፍቆት አስተቃቀፉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከቢታንያ ተነስቶ ኢየሩሳሌም ሲገባ አረጋዊያንና ህጻናት በዘንባባ ቅጠል 'ሆሳዕና በአርያም' እንዳሉት ሁሉ፣ ዶክተር ዐብይ አስመራ አየር ማረፊያ(የቀድሞው ዮሐንስ አራተኛ) ከተፍ ሲል ኤርትራውያን እናቶች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ልጃቸውን በሐሴት ተቀበሉ። ክብርና ደስታ በወጠረው ሳቂታ ድባብ የሳቀ ፈንደሻ ረጩ። ሸሚዝ አዘወታሪው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካለወትሯቸው ሱፋቸውን አድረገው ኢትዮጵያዊ ወንድማቸውን በፈገግታ አቀፉ። የ72 ዓመቱ አዛውንት ፖለቲከኛ የ42 ዓመቱን ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር የመደመር እሳቤ በፍቅር ተቀብለው ኮስታራ ፊታቸውን አፍግገው ታቀፉት። አንዳንዶቹም የደስታ ዕንባ አነቡ። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችው ብቸኛዋ የአፍሪቃ መዲና የ‘ጓል አስመራ’ ጎዳናዎች ደጃቸውን ለረገጠ ናፋቂያቸው ‘ቤት ለእንግዳ’ አሉ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ በማውለብለብ ‘መርሐባ’ አስነበቡ። ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው የሰላም እጃቸውን አውለበለቡ፤ የፍቅር መዳፋቸውን ዘረጉ። የበዓሉ ግርማ ምዕናባዊ ዘንባባዎች በዕውን በፍቅር ነፋስ ተወዛወዙ...... ዘመን በአፈራው ቴክኖሎጂ ይህን ትዕይንት የተመለከቱ የካፌው ተስተናጋጆች የስፍራው ድባብ የቴሌቪዥን መስኮት ዘልቆ የተስተጋባባቸው ይመስላል። መተቃቀፉ፣ የልዑካኑና አገሬው ፈገግታ፣ ሐሴቱ፣ የፍቅርና ይቅርታ መንፈሱ፣ የአቀባበል ስሜቱ.... ውስጣቸውን ኮርኩሮት ይመስል ይቁነጠነጣሉ። ፊታቸው በደስታ ወግጎ በግርምት ከንፈራቸውን ይመጣሉ፤ ጭንቅላታቸውን ይወዘውዛሉ። ምናልባትም ለ12 ዓመታት የስልክ ግንኙነት የናፈቃቸው ዘመዳሞች ተደዋውለው ተላቅሰው ይሆናል። በአካል ለመገናኘት የተስፋ ጥሬያቸውን የቆረጠሙበት ዕለት ይሆናል።'መጥፎ ታሪካዊ ክስተት' የነጣጠላቸው ቤተሰቦች ሌላ 'መልካም ታሪካዊ ክስተት' ዳግም ሊደምራቸው መሆኑን ታዘቡባት - የትናትናዋን ዕለት.... ዶክተር አብይ 'በይቅርታ እንደመር' አሉ። ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ጥሪውን ተቀበሉ። ተወካዮቻቸውንም አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ላኩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደቃላቸው ልዑካኑን እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ አስተናገዱ። በመስተንግዷቸው ወቅትም በፈገግታ በታጀበ ንግግራቸውም ሁሉን ወገን አስደመሙ። 'መጭውን አዲስ ዓመት አዲሴ አበቤዎች አስመራ፣ አስመሬዎች አዲስ አበባ ለማክበር ተዘጋጁ' በማለትም እንደቀልድ ተናገሩ። ከቀናት ማግስት ግን የ2011 ረቂቅ በጀት በፓርላማ ካፀደቁ በኋላ ልዑካቸውን መርተው በክረምት ኤርትራ ገቡ። ኤርትራ ለማንም አድርጋው የማታውቀውን ደማቅ አቀባበል ስቃ ተቀበለች። በመልካም ሰበር ዜና ለወራት እያስኮረሸሙ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝናባማዋ የሐምሌ መባቻ የፍቅርና ይቅርታ የመደመር መርከባቸው አበሰሩን። ዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለዓመታት ያዜመለት የያስተሰርያል፣ ዳህላክ ላይ ልስራ ቤቴን፣ ፊዮሪና፣ ኡኡታዬ... ዜማዎቹ ለወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች ያቀነቀነው ምኞት በጊዜው መፈጸም ጀመረ። እናም፡- "ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳኤ፣ በአንድነት ከገባን በፍቅር ሱባኤ...." እንዳለው ድምጻዊው በዶክተር ዐብይ አባባል ለዓመታት የነበረው 'ሞት አልባ ጦርነት' በፍቅር ሱባኤ ተፈታ። የሁለቱ አገሮች 'ድንበር' በ'ፍቅር ድልድይ' ተተካ። የሁለቱ አየር መንገዶች፣ ወደቦች፣ መርከቦች በጋራ እንደሚሰሩ መሪዎቹ አበሰሩ። ህዝቦች እንዲንቀሳቀሱ፣ ኤምባሲዎች እንዲከፈቱ፣ ለሁለት አስርታት የተቆሰቆሰ ግጭት ወደ አዲስ ፍቅር፣ ዜጎች በጋራ ሰርተው በጋራ ወደሚለወጡበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን ተናገሩ። 'ከዚህ በኋላ ምንም ይምጣ ምንም ችግራችንን አብረን እንወጣዋለን' አሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ። ዶክተር ዐብይም "ውጊያ መስማት ይበቃናል። እኛ ሰላም ከሆን ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ይዘንባል" በማለት የሁለቱን አገሮች የሰላም ዝናብ በሰላምና መረጋጋት ድርቅ ለተመታውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተስፋ አረስራሽ ዝናብ እንደሆነ ዳግም ሰበኩ። 'ጊዜ ለኩሉ' እንዲሉ ዐብይና ኢሳያስ በአንድ ረከቦት በተሰደሩ ሲኒዎች ከአንድ ጀበና ከተቀዳ ቡና ተጎነጩ። ቢላ ተጋርተው ዳቦ ቆረሱ። በፍቅር ሱባኤ፤ በፈገግታ በአንድ ማዕድ ራት ተቋደሱ ..... ዶክተር ዐብይ የርዕሰ መንግስትነቱን መንበር ከተቆናጠጡ ድፍን መቶ ቀናት ሊሆናቸው ሁለት ቀናት ብቻ ቀሩ/ለመቶ ሁለት ቀሪ። ከበዓለ ሲመታቸው ንግግር ጀምሮ እያፈለቁት ባለው ሃሳብና እየወሰዷቸው ባሉት እርምጃዎች "መቶ ሚሊዬን"ን ለዘለለ ተመሪ ሕዝባቸው ብቻ አይደለም፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ቀልብ እንደሳቡ፣ ከ"ዐይን ያውጣህ"እንደተባሉ ቀጥለዋል። ለሁለት ዓመታት በተቃውሞ ስትናጥ የነበረች አገር፣ የወደፊት እርምጃዋ ይመሰቃቀላል ተብሎ በተንታኞች የተነገረላት ኢትዮጵያ በሶስት ወራት ውስጥ አቅጣጫዋን ለወጠች። መንግሥታዊ ተቃውሞዎች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ማዕበል ተቀየሩ። ከአሳዛኝ ሰበር ዜናዎች በአንጻራዊነት አስደሳች ሰበር ዜናዎች መስማት ተቻለ። እናም ብዙኃኑ ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር አስተሳስብ አብዮት ተናወጠ። ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገር የመንግስት ተቃዋሚዎች ሳይቀር በዘረጉት "የፍቅርና ይቅርታ ጃንጥላ" ተጠለለ። ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበዓለ ሲመታቸው አንስቶ ባራመዱትና በወሰዱት የማይናወጥ በአገር አንድነት አቋም ይመስላል። "የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዚህ በኋላ መምራት የሚቻለው በፍቅርና በዴሞክራሲ ነው። መገዳደል ይቻል ይሆናል እንጂ አያሻግርም"አሉ። ሚሊየኖች አደባባይ ወጥተው ድጋፍና አድናቆታቸውን ሲገልጹላቸው እርሳቸውም 'ጎንበስ' ብለው እጅ ነሱ። በ98 ቀናት ቆይታቸው የዶክተር ዐብይ ዐብይ ክንውኖች በጥቂቱ…. አንድ፡- ካቢኒያቸውን ባዋቀሩ ማግስት ቀደም ሲል የተጀመሩ የእስረኞ ማስፈታት ጅምሮችን ጥግ ድረስ ዘለቁበት። ይህ ደግሞ በተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ግለሰባዊ ነፃነት ሳይሆን ቤተሰባዊና አገራዊ ይቅርታው በለጠ። ሕዝብ የጮኸላቸው ግለሰቦች ሲፈቱ ሕዝቡም ጮኾ ተቀበላቸው። በተለያየ መንገድና ጥፋት ተብሎ በተገለጸ ወንጀል የታሰሩ ፖለቲከኞችን ከእስር መፍታት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አብሮነት ቤተ መንግስት እየጠሩ የፍቅር ግብር አበሉ። ከኢህአዴግ ጋር ዐይንና ናጫ የነበሩ ግለሰቦች በዶክተር ዐብይ ዘመን በይቅርታና ፍቅር ተደመሩ። ከዓመታት እስር የተፈቱት ጀኔራል አሳምነው ጽጌ "ሙሴ እስራኤላዊን በአርባዎቹ መጀመሪያ ዕድሜው ነጻ አወጣ፤ ዶክተር ዐብይም በአርባዎቹ መጀመሪያ እድሜው ነጻ አወጣን" በማለት ከነብዩ ሙሴ ጋር አነጻጽረው አወደሷቸው። አንዳንድ ጋዜጦችና ግለሰቦችም "ኢትዮጵያዊ ሙሴ" በማለት አሞካሹ። ሁለት፡- ገና ቤተ መንግስትን ከመርገጣቸው በአራቱም ማዕዘናት አገራቸውን ዞሩ። የመጠራጠር ነፋስ የጎበኘውን ሕዝብ፤ ሕዝቡ ራሱ ባለው ፀጋና ስነልቦና በኢትዮጵያዊነት አወያዩት። በሕዝባዊ ምክክሮሽ መድረኮች ወጣቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣  የኃይማኖት አባቶችና ፖለቲከኞች ከአንደበተ ርዕቱው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በግልጽ ተወያዩ። የሃሳብ ብዝኃንነትን በመቻቻል፣ በመከባበርና በመደመር አብረን ለሺህ ዓመታት መስዋዕትነት ለተከፈለባት አገር በአንድነት ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ። ሁሉም ወገን በአዎንታ ተቀበለው። ከካቢኔያቸው፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተመካከሩ። በየመድረኩ ሃሳባቸውን በሚገልጹበት አንደበትም የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ የሳቡ ቃላትና ሃሳቦች መነጋገሪያ ሆነው ቀጠሉ። ሦስት፡- በአገር ውስጥ እርምጃዎች በኋላም ጎረቤት አገሮች ደጃፎችን ጎበኙ። ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ትናንት ደግሞ ኤርትራ ተዘዋወሩ። አላበቁም፤ አዋሳኝ ባልሆኑ ወሳኝ ጂኦ ፖሊተካል አገሮች ካለ እረፍት ጉብኝታቸውን ቀጠሉ። የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ የግብጽና ኡጋንዳ ደጃፍ ረገጡ። በሶስት ወራት ያከናወኑት የውጭ ጉዞ ታዲያ የተለመደ ተራ ዲፕሎማሲ አልነበረም። በጎረቤትና በአረብ አገሮች የታጎሩ በሺዎች የሚቀጠሩ ኢትዮጵያዊያን እስረኞችን ነጻ አውጥተው ይዘው መጡ። አንዳንዴም በራሳቸው አውሮፕላን አብረው አሳፍረው (የግብጹን ልብ ይሏል) በቃላት በማይተመን ፍቅር እየለገሱ አገራቸው ሰማይ ስር አደረሷቸው። አንድም ሰው ይሁን፤ ከባዕድ አገር እስር ነጻ ወጥቶ ለአገር የመብቃትን ስሜት እንኳን እንደኔ አይነቱ ታዛቢ ነጻ የወጡ እስረኞችም የሚገልጹበት ቃል ያለ አይመስለኝም። ከደስታ ስካርና እንባ በቀር!! በምንም የማይወዳደረውን ሰብዓዊ ድርጊታቸው አነሳን እንጂ ጠቅላይም ሚኒስትሩ በዞሩባቸው አገሮች በኢኮኖሚውና ፖለቲካዊ ዘርፍ ያራመዷቸው ሃሳቦችም አጀብ አስብለዋል። በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወጣት ተራማጅ መሪ ተሰኝተዋል። ለወደፊታ አፍሪካ ተስፋ የተጣለባቸው አርዓያ መሪ አድርጓቸዋል…. አራት፡- እንደአብዮት ያቀጣጣሉት "የመደመር እሳቤ" እንዲሰምር የመንግስታት ተቋማት ኃላፊዎችን በአዲስ አዋቅረዋል። ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችና ሌብነት ለአገር እድገት ፀርነቱን ብቻ ሳይሆን የሚወገድበትን መንገድ መቀየስ ጀምረዋል። በተመሳሳይ አገሪቷ ለገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትሔነት በእርሳቸው አመራር ዘመን በተለይም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ አዲስ ውሳኔ አሳልፈዋል። ይህም በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ገጹ ግራ ቀኙን ወገን በሃሳብ ያናወጠ ትልቅ እርምጃ ነበር። አምስት፡- የኢትዮ ኤርትራን በተመለከተ ለዓመታት ተፈጻሚ ያልነበረው የአልጀርስ ስምምነት ለተግባራዊነቱ በአዲስ መወሰኑን ይፋ አደረጉ። ሁለቱ ሕዝቦች ለሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያሳለፉት ቆይታ ለማንም እንዳልበጀ፤ የጥላቻና የታሪክ ቁርሾ በይቅርታና በፍቅር አዋዜ እንዲለወስ ጥሪ አቀረቡ። የፍቅር ድልድይ ጥሪያቸውም ተገንብቶ ፍሬ አፈራ። ለዓመታት ያልሰመረና ለየትኛውም ሕዝብ ያልበጀ የሁለትዮሽ ግንኙነት በሐምሌ ፀሐይ ተሻረ። የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ደግሞ ከሌሎች አገሮች በተለዬ የማንንም ቀልብና ፍላጎት የሳበ ብቻ አይደለም፤ በደስታ ፈንጠዝያ ማሳበዱ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ስድስት፡- ስንሰማው ስናየው የኖርነው የኃይማኖት አባቶች መሪዎችን ሲያስታርቁ ነው። ዶክተር ዐብይ ግን ኃይማኖተኛ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኃይማኖት አባቶች ምዕመኑን ስለፍቅር፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ አንድነት፣ ስለ መከባበርና አብሮነት በአጠቃላይ ለኢትዮጵያዊነት እሴቶች እንዲሰበኩ ብቻ አይደለም የተነጋሩት። ግና በአንድ ኃይማኖት ጥላስር የተከፋፈለ ሀሳብ የሚያራምዱ ቡድኖች እርስ በእርሳቸው እንዲታረቁ መሰርት ሃሳብ ጥለዋል። በእስልምና መጂሊስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ያቀረቡት ሃሳብ አንዱ ከስንት አንድ የሚገኝ ከቅን መሪ ሰናይ ግብር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወታደራዊ መስክ፣ በኪነ ጥበብ፣ በአመራርነት ያላቸው ዕውቀትና ክህሎት ምናልባትም ከምናውቀው ፖለቲከኛ ባህሪ አልፈው ሰው ሰው እንዲሸቱ አግዟቸው ይሆን? ያስብላል.... እነዚህና ሌሎች እርምጃዎች የቅርብ የሩቅ ኢትዮጵያውያንን ጮቤ አስረገጠ። የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ ዲያስፖራዎች፣ ተፈካካሪ ፓርቲዎች፣ በአሰተሳስብ ጽንፍ የወጡ ብረት ያነገቡ ድርጅቶች ሳይቀሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍቅር ጥሪ ተማረኩ። የምዕራባዊያን አገሮች ከተሞች ሲደረጉ የኖሩ ተቃውሞዎች በዶክተር ዐብይ የወራት ስልጣን ዘመን ወደ ድጋፍ ተቀየሩ። ይሄን ደግሞ በአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ የወጣ አንድ ሰልፈኛ እንደተናገረው ዛፎች፣ አደባባዮች፣ ሕንጻዎች መታዘባቸው አልቀረም። በዋሽንግተኑ የድጋፍ ሰልፍ የአንድ ወር መንታ ሕጻናትን ይዛ ሰለፍ የወጣችው አራስ እናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ጥግ ምን ድረስ እንደሆነ ጉልህ ማሳያ ነው። ዘመናቸውን በገዥው ፓርቲ/ኢህአዴግ ትችትና ተቃውሞ ሲያራምዱ የነበሩ ጉምቱ ምሁራንና ፖለቲከኞችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍቅርና የመታረቅ ቋንቋ እጅ ሰጡ። በሰላ ትችታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማርያም "አብይ አህመድ የሚቆጣጠሩት የፍቅር ባቡር ፍሬን የለውም። የሚያቆመውም ኃይል የለም። ስለዚህ መሳፈር ብቻ ነው ያለብን። የፍቅር ባቡሩ የሚያደርሰን ኮረብታ ላይ የተሰራች እያልኩ ሁልጊዜ የምመኛት ኢትዮጵያ አለች፤ እዛ ስር ነው የሚያደርሰን። እዚሀ በምንደርስበት ጊዜ አናጢውም፣ ግንበኛም ምኑም እቃውን እየያዘ ብቻ ሂዶ መገንባት ነው" ብለዋል። አንጋፋው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም "እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይና  መከራ አይቶ ዓብይን ፈጠረውና ወደ ኢትዮጵያ ላከው" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለምንም እረፍት ለአገራቸው እያደረጉ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል። ይሄም ፕሮፌሰሩ ባሳለፉት ሶስት ሰርዓተ መንግስት ውስጥ አንድ አገር መሪ ሲያደንቁ የመጀመሪያቸው ይመስለኛል። ሌላው በሰኔ አስራ ስድስቱ የአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ ተጎድቶ ሆስፒታል የገባና አንድ እግሩን ያጣው ውጣት "ብሞትም አይቆጨኝ፣ እባካችሁ ከጎኑ ሁኑ" በማለት ለመገናኛ ብዙሃን ያስተላለፈው መልዕክትም ሌላው ልብ ሰባሪ ጉዳይ ነው። ከኪነ ጥበብ ሰዎች መካከልም ቴዲ አፍሮም "ኢትዮጵያዊነትንና ይቅር መባባልን ይዘው ብቅ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ባልደረቦቻቸው አዲስ በሚባል የስልጣን ቆይታቸው በወሰዳቸው በጎ እርምጃዎችና ላሳዩን ኢትዮጵያዊ አለኝታነት፣ አጋርነት ማሳየትና ከጎናቸው መቆም ጊዜው የሚጠይቀው አስፈላጊ ተግባር ነው" በማለት ስሜቱን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጋርቷል። ትናንትና ቅዳሜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርቲሲ ተመራቂ ተማሪዎች በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ያሰሙት የድጋፍ ድምጽና ያስነበቧቸው የፍቅር ጥቅሶች አገር ተረካቢው ትውልድ ያለውን ለኢትዮጵያዊነትና ለአገር አንድነት ምን ስሜት እንዳለው የሚጠቁም አንደምታ ይመስለኛል። በወቅቱ በስፍራው የተገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርቲ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ አስተማሪው ፕሮፌሰር አህመድ አሊ አህመድ "ትልቅ ነገር ነው። ትልቅ ተስፋ ነው። ለአገርም ለአህጉሩም፣ ለዓለምም ትልቅ ተስፋ ነው። እኔም ከፍተኛ ምኞትና ደስታ ነው ያጫረብኝ፤ ትልቅ ነገር ነው" ይሄ በማለት ነበር ትዝብታቸውን ያጋሩኝ። ሐዋን መለስ በሒሳብ ትምህርት ክፍል አራት ነጥብ ይዛ የተመረቀች የወርቅ ተሸላሚ ናት። "ዶክተር አብይ ጥሩ መሪ ይመስለኛል። እስካሁን እየሰራ ያለው ስራ በጣም ጥሩ ስራ ነው። ተማሪዎችን ዕውቅና እሰጣለሁ፤ ምናምን ያለው ነገር አለና እስካሁን እየሰራ ያለው ደስ የሚል ስራ ነው፤ ሁሉም ሰው ይወደዋል ብዬ አስባለሁ"  አለችኝ በፈገግታ። ብቻ በፍቅር ባቡር ከምንመኛት አገር ማማ ላይ ያድርሰነ! ያስብላል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም