መቀሌ ዩኒቨርስቲ ለ1 ሺህ 400 ወገኖች የምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌ ዩኒቨርስቲ ለ1 ሺህ 400 ወገኖች የምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ
ሽሬ ሰኔ 17/12 (ኢዜአ) መቀሌ ዩኒቨርስቲ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ለ1 ሺህ 400 የኩናማ ብሄረሰብ ተወላጆች የምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ ።
ዩኒቨርስቲው ድጋፉን የሰጠው በትግራይ ምዕራባዊና ሰሜናዊ ምዕራብ ዞኖች ለሚገኙ የኩናዋ ብሄረሰብ ተወላጆች ነው።
ዩኒቨርስቲው የለገሰው 400 ምርጥ የማሽላ ዘር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችል የዘር እጥረት ለማቃለል ታስቦ መሆኑን የዩኒቨርስተው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፎትየን አባይ በርክክቡ ስነ ስርዓት ላይ ገልፀዋል።
በሁለቱም ዞኖች ለሚገኙ የብሄረሰቡ ተወላጆች ዛሬ የተበረከቱ ድጋፎች ከፍተኛ ምርት የመስጠት አቅም ያላቸውና ''መልካምና ደቀባ'' የተባሉ የማሽላ ዘሮች ናቸው ብለዋል።
ምርጥ ዘሮቹ ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት በ322 ሺህ ብር ወጪ የተገዙ መሆናቸውን ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል ።
በኩናማ ብሔረሰብ በብቸኝነት የሚመረተው “ብልቱግ” የተባለ ሰብል የሚሰጠው ምርት ለማሳደግና ይበልጥ ብሄረሰቡ ከዚሁ ሰብል ተጠቃሚ ለማድረግ የምርምር ስራ ለማከናወን ዩኒቨርስቲው እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተሰጠው የምርጥ ዘር ድጋፍ 1 ሺህ 400 የብሄረሰቡ አባላት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ናቸው።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የተበረከተው ይኽው የማሽላ ምርጥ ዘር የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ምርጥ ዘሩ በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተሞክሮ በአማካይ ከአንድ ሄክታር 45 ኩንታል ምርት መገኘቱን ነው የገለፁት።
ለዘንድሮው የመኽር አዝመራ እስከ አሁን ድረስ 68 ከመቶ የምርት ግብአት በአርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ መደረጉንም ጠቁመዋል ።
በምርጥ ዘር ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኩናማ ብሄረሰብ ተወካይ አቶ ብርያነ ኬኙ እንዳሉት በአስቸጋሪ ወቅት ላይ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ያበረከተው ድጋፍ ልዩ ስሜት ፈጥሮብናል ብለዋል።
በትክክለኛ ጊዜ የተሰጠ የማሽላ ዘር ብሄረሰቡ ለምግብነት እንዳያውለው ጥብቅ ክትትል በማድረግ ለታለመለት አላማ እንዲውል ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በየዓመቱ 79 ሺህ 350 ሄክታር መሬት በማሽላ ዘር እንደሚሸፈንና በየአመቱ በአማካይ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚሰበሰብ የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ክብሮም ብስራት ናቸው።
በዘንድሮው የመኽር አዝመራ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማሽላ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል ።