የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባብስ መልኩ ለማሟላት ይሰራል--የገንዘብ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባብስ መልኩ ለማሟላት ይሰራል--የገንዘብ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) በቀጣዩ ዓመት የበጀት ጉድለት የዋጋ ግሽበትን በማያባብስ መልኩ ለማሟላት እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2013 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ዙሪያ ያዘጋጀው የአስረጂዎች መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በረቂቅ በጀቱ ላይ ከገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ሌሎች የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግሥት ለ2013 በጀት ዓመት 476 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ያቀረበ ሲሆን 126 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ይኖረዋል።
የበጀት ጉድለቱንም 48 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከውጭ ከሚገኝ እርዳታና ብድር፣ 77 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን አቅዷል።
ከምክር ቤቱ አባላት በአገር ውስጥ ብድር የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የቀረበው እቅድ የዋጋ ግሽበትን አይጨምርም ወይ? በምን አይነት መልኩ ነው ብድሩ የሚከናወነው? የሚል ጥያቄ ተነስቷል።
በተጨማሪም ረቂቅ በጀቱ ከበጀት ድልድል ፍትሐዊነትና የልማት ጥያቄዎች አንጻር እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄም ቀርቧል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በሰጡት ምላሽ የአገር ውስጥ ብድርን ከግምጃ ቤት ሽያጭና ከብሔራዊ ባንክ በመበደር ለመሙላት እቅድ እንዳለ ገልጸዋል።
አብዛኛውን ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ለመሙላት እቅድ መያዙንና ይህም የዋጋ ንረት እንዳይከሰት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የቀጥታ ብድር የሚጠየቀው ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ በቂ ካልሆነ ብቻ እንደሆነም አመልክተዋል።
ከውጪ የሚገኘው እርዳታና ብድር በበጀት ዓመቱ ፈሰስ የሚደረጉ የፋይናንስ አቅርቦትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ግምገማ ተደርጎበት በጥንቃቄ እንደተዘጋጀም ገልጸዋል።
የበጀት ፍትሐዊነት ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚነሳ እንደሆነ ገልጸው፤ ''ከዚህ በፊት ጥናት ተጠንቶ ምክክር የተደረገበትና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የጋራ ሥራ የሚጠይቅ ነው'' ብለዋል።
ከረቂቅ በጀቱ 271 ቢሊዮን ብር ከታክስ ለማሟላት መታቀዱንና ለዚህም የታክስ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህም ረገድ የታክስ አሠራር ሥርአቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የበጀቱ ዋነኛ ትኩረት የተገኙ የኢኮኖሚ ለውጦችን ባሉበት እንዲቀጥሉ ማድረግና በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት የሚፈጠረውን ተፅእኖ በመቀነስ ኢኮኖሚው በተነቃቃ መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ደመቀ የበጀት ድልድል የሚከናወነው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ቀመር አማካኝነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
''የፌዴራል በጀት የሚመደበው የተቀመጡ ተልዕኮዎችና ግቦችን ከማሳካት አኳያ ታሳቢ ሊደረግ ይገባዋል'' ብለዋል።
አብዛኛው በሚመደበው በጀት የሚከናወኑ ሥራዎች በክልሎች እንደሆኑና ከዚህም አኳያ ለልማት ሥራዎች አስፈላጊው በጀት መመደቡን ዳይሬክተሩ ጨምረው ተናግረዋል።