የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዋና ዋና ስራዎችን ግምገማ በማጠናቀቅ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዋና ዋና ስራዎችን ግምገማ በማጠናቀቅ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2012 በጀት ዓመት የታቀዱ ዋና ዋና ስራዎችን በመገምገም ለቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ትናንት የጀመረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።
በትናንትናው ዕለት የኢኮኖሚ ዘርፍ ስራዎች ተገምግመው ማጠቃለያ እንደተሰጠባቸው ያስታወሱት አቶ ንጉሱ፤ በዛሬው ዕለት የሰላምና ጸጥታ፣ የማህበራዊ እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራዎች መገምገማቸውን ገልጸዋል።
ህግ በማስከበር ሰላምና ጸጥታ በማጎልበት የህብረተሰቡን ተደራሽነት በማረጋገጥ ረገድ ተጠናክረው መሰራት ያለባቸው ተግባራት መለየታቸውን ገልጸዋል።
የተገኘው ውጤት በቀጣይ ለህብረተሰቡ የሚደርስ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ በግምገማው ሰፊ ውጤት መምጣቱና እጥረት የታየባቸው ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ ተቀምጦባቸው ግምገማው መጠናቀቁን አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ ትናንት በነበረው መድረክ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተብለው በተለዩ ዘጠኝ መስሪያ ቤቶች አፈጻጸም ገምግሟል።
ግምገማው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ዋና ዋና ዕቅዶች አፈጻጸም፣ የገጠሟቸው ችግሮች፣ መልካም ተሞክሮዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነበር።