ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስለ አባይ ወንዝ እውነታዎች ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ብዙ መስራት እንዳለባት ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ስለአባይ ወንዝ እውነታዎችና የመጠቀም መብቷን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ብዙ መስራት እንዳለባት ተገለጸ።

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ መነሻ መሆኗን በቅርቡ ያወቁ የአረብ ሊግ አባል አገሮች አመራሮች መኖራቸውም ተጠቁሟል።

ኢዜአ ከመምህር ዳኒኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ከኡስታዝ ያሲን ኑሩ እና ከዘማሪ ሶፊያ ሽባባው ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ''ግብጽ እያራመደችው ያለው አቋም ከሃይማኖትም፣ ከፖለቲካም፣ ከስብዕናም አኳያ ቢታይ ፍትሃዊ አይደለም'' ሲሉ አስረድተዋል።

የአባይ ወንዝ የልማት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የማንነትና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ  መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም በሃይማኖታዊ መፅሃፍትና ታሪኮች ላይ ሲታይ ወንዙ ኢትዮጵያዊያን ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ህይወትን የጀመሩበት እንዲሁም ስልጣኔን ለቀሪው አለም ያስፋፉበት የታሪክ  መሰረት መሆኑንም አስረድተዋል።

ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ኢትዮጵያ በወንዙ የመጠቀም መብቷን ለአለም ማህበረሰብ በተገቢው ልክ እንዳላስረዳች ገልጸዋል።

በወንዙ ላይ የመጠቀም መብቷን ለመከላከል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሲሰራጭ እንደነበረ የማስረዳት የቤት ስራ እንደሚጠብቃት ገልጸው፤ "ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ጭምር ጠቃሚ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ለዓለም ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል።

ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ አለመጠቀም የሚያስጠይቅ መሆኑን በቅዱስ ቁርዓን ላይ መቀመጡንም ጠቁመዋል።

ዘማሪ ሶፊያ ሽባባው በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ግብፅ የምታራምደው 'እኔ ብቻ ልጠቀም' አቋም ከሃይማኖትም፣ ከፖለቲካም፣ ከሰብዓዊነት አስተሳሰብ የወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ፈጣሪ የሰጣትን ሀብት መጠቀም አይቻልም ማለት ከባርነት ለይቼ አላየውም “ ብለዋል ። 

በሁሉም መስክ ያለ ኢትዮጵያዊ የቦንድ ግዢ መፈጸም ብቻ ሳይሆን የሙያ ድጋፍ ጭምር ማድረግ እንደሚጠበቅበት የገለጹት ደግሞ መምህር ዳኒኤል ሰይፈ ሚካኤል ናቸው። 

ሁሉም ሃይማኖቶች በደልንና ራስ ወዳድነትን እንደማይሰብኩ የገለፁት ተወያዮቹ፤ ኢትዮጵያ የያዘችው 'ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ' አቋም በሃይማኖትም የሚደገፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

''ግብፅ የአባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም ማንኛውንም አጋጣሚ ልትጠቀም እንደምትችልና ለዚህም ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንና ህብረታችን ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል'' ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በገንዘብና በሙያ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር የኢትዮጵያን መብትና ተጠቃሚነት ሊያስጠብቁ የሚችሉ መረጃዎችን ለአለም ማስረዳት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም