ፕሮጀክቱም ያልቃል፤ ሕዝቡም የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮጀክቱም ያልቃል፤ ሕዝቡም የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በከፍተኛ ንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ በሆነ የውሃ ሃብት አጠቃቀም መሰረት የሕዳሴ ግድቧን እየገነባች ቢሆንም ግብጽ በምታራምደው ተለዋዋጭ አቋም መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ዓፈ-ጉባዔው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹትም የሕዳሴው ግድብ የታሰበለትን ግብ እንዳይመታ ትክክል ያልሆኑ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በቅርቡ የዓረብ ሊግ ያወጣው መግለጫ የተሳሳተና የኢትዮጵያን በውሃው የመጠቀም መብት ያላገናዘበ መሆኑን የሚያሳይ አቋም በምክር ቤቱ መውጣቱን አስታውሰዋል።
እንደ ዓፈ-ጉባዔው ገለጻ አሁንም በሌሎች አገራት የሚካሄዱ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን መግታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ምክር ቤቱ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱን ከዳር በማድረስ ሕዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ የሚገነባው ግድብ በፍትሃዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ የተመሰረተ እንጂ 'ሌሎች ወንድሞቻችንን ለመጉዳት ታስቦ የሚከናወን አይደለም' ብለዋል።
ይህንኑ ጉዳይ ለተለያዩ አካላት ለማስረዳት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ብዙ አገራት እየተረዱን ነው ብለዋል ዓፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ።
የውሃ ሙሌት ሥራው ከመጀመሩ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአካል በመገኘት ግድቡ የደረሰበትን ሁኔታ እንደሚጎበኝ አፈ-ጉባዔው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ 86 በመቶውን ብታበረክትም በጋራ የመጠቀም መርህ ተከትላ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት ለውሃ ሙሌት በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች።
የወንዙ ከፍተኛ ተጠቃሚዋ ግብፅ ግን በየዓመቱ ከአስዋን ግድብ በትነት የሚባክነውን ያህል ውሃ እንኳን ኢትዮጵያ ልትይዝ አይገባም የሚል ግትር አቋም ይዛለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በግድቡ ላይ የሚያደርጉት ድርድር የቴክኒክ ጉዳይ ሆኖ ሳለም ግብጽ ግን የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ አሁንም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቧን ቀጥላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በድርድር ሰበብ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚኖራትን የመልማት መብት የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል አረጋግጠዋል።