በአማራ ክልል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ266 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ266 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
ባህር ዳር ሰኔ 17/2012( ኢዜአ ) በአማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ266 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ገቢው የተገኘው ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላከ ከሁለት ሚሊዮን 300ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች እንደሆነ የቢሮው የግብይት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አበባው ውቤ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከባለሀብቶች ከተላኩት ምርቶች ውስጥ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ነጭና ቀይ ቦለቄ እንዲሁም ማሾ ይገኙበታል።
በበጀት ዓመቱ ወደ ውጪ ከሚለኩ ምርቶች 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ ከዚህ ውስጥ የ11 ወራት አፈጻጸም የእቅዱን 88 ነጥብ 9 በመቶ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዓመቱ የነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣልና የኮሮ ቫይረስ መከሰት የገቢ እቅዱን ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ እንዳደረገው ጠቁመዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሐሙሲት ከተማ የሰሊጥ አቅራቢ ነጋዴ ቄስ አደራጀው ከፍያለው እንዳሉት አንድ ኩንታል ሰሊጥ ከአምራች አርሶ አደሮች እስከ አራት ሺህ 200 ድረስ በመግዛት እያቀረቡ ነው።
ገዝተው ያቀረቡትን 200 ኩንታል ሰሊጥ ለኢትጵያ ምርት ገበያ በአራት ሺህ 500 ብር እንዳስረከቡ ተናግረዋል።
አንድ ሺህ 500 ኩንታል ሰሊጥ ከአርሶ አደሩ በኩንታል እስከ አራት ሺህ 100 ድረስ ገዝተው ማቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ከተማ የሰሊጥ ነጋዴ አቶ ማራቸው ሙጨ ናቸው።
ሆኖም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የግብይት ስርዓት በመዘርጋቱ ባለፈው ዓመት ይረከብበት ከነበረው በኩንታል እስከ 500 ብር ድረስ በመቀነስ እየተረከበ ነው ብለዋል።
ይህም የትራንስፖርት፣ የማበጠሪያና ሌሎች ወጪዎችን ባለማካተቱ ለኪሳራ እያጋለጣቸው መሆኑን ተናግረው፤ መስተካከል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጎንደር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ባየልኝ ዘራዕይ በበኩላቸው ምርቱን የሚረከቡት እንደ ሀገር ወጥ በሆነ ግብይት ከአቅራቢ ነጋዴዎች መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ምርት ገበያው ከነጋዴው የሚረከብበትና ለውጪ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ተመጣጣኝ አልነበረም ብለዋል።
ከነጋዴው ማህበረሰብ በውድ እየተገዛ ለውጪ ገበያ ሲቀርብ አዋጪ ሆኖ ባለመገኘቱ ንግድ ሚኒስቴር አለም አቀፍ ገበያውን ከግምት ያስገባ መመሪያ በማውጣቱ በዚያ መሰረት ግብይቱ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም የንግድ ሚኒስቴር አለም አቀፍ የግብይት ስርዓቱን መሰረት አድርጎ በሚያወጣቸው መመሪያዎች መሰረት ግብይቱ ይከናወናል ብለዋል።