የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ11 ወራት ውስጥ 352 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ11 ወራት ውስጥ 352 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ11 ወራት ውስጥ ከክፍያ መንገድ አገልግሎትና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከ352 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገለጸ።
በ2012 በጀት ዓመት ባለፉት 11 ወራት ከመደበኛ አገልግሎት የትራንስፖርት ክፍያና ከተለያዩ ምንጮች ስለሰበሰበው ገቢ ኢንተርፕራይዙ መግለጫ አውጥቷል።
እንደ መግለጫው፤ ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የአዲስ አበባ-አዳማ እና ድሬዳዋ-ደዋሌ ክፍያ መንገዶች በ11 ወራት ውስጥ ከ8 ሚሊዮን በላይ የትራፊክ ፍሰቶችን አስተናግደዋል።
መንገዶቹ 24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ከትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ 323 ሚሊዮን 762 ሺህ 84 ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች ደግሞ 28 ሚሊዮን 738 ሺህ 303 ብር ገቢ ተገኝቷል።
ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የገቢ ምንጮች ፍጥነት መንገዶቹን ተከትሎ የማስታወቂያ ቦታ ኪራይ እንዲሁም የተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ አገልግሎቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ኢንተርፕራይዙ የመንገዱን ደህንነት ለማስጠበቅ በተለያዩ ቦታዎች የመንገድ አጠቃቀም ትምህርት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስጠቱን ገልጿል።
በዚህም የትራፊክ አደጋ ክስተትን ከአምናው አንጻር በ50 በመቶ ያህል መቀነስ ተችሏል።
ገቢውንም ለማሳደግ የመረጃ ቋት አቅም ማሳደግና የመንገድ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ በማከናወን የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ መሆኑን አመልክቷል።
አገልግሎት ላይ ያሉ የአዲስ አበባ-አዳማ እና ድሬዳዋ-ደዋሌ ክፍያ መንገዶች ለተጠቃሚው የ24 ሰዓት እየሰሩ መሆናቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ አዳማ እና የድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን የሞጆ-ሐዋሳ የክፍያ መንገድ በግንባታ ላይ ነው።