ቀጥታ፡

በድርድር ወቅት የግብጽ ወገን የተለያዩ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣል--የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

በህዳሴ ግድብ ድርድር ወቅት የግብጽ ወገን የተለያዩ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር ተገለጸ

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ባደረጓቸው ድርድሮች የግብጽ ወገን የተለያዪ አጀንዳዎችን እያቀረበ ውይይቱን ውጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

ግብጽ የራሷን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ትሰራ እንደነበርም አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን ከአልጄዚራ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከአልጀዚራ አረብኛ ስርጭት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ትናንት ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓም ማምሻውን በጣቢያው ተላልፏል።

በዚሁ መሰረት የአልጀዚራ የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ጣሃ ተወኩል በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄዎች አቶ ገዱ ምላሽ ሰጥተዋል።

ግብጽ በጎረቤት አገሮች ላይ የጦር ካምፕ ለመመስረትና የኢትዮጵያን ደህንነት ለመፈታተን የምታደርገን ጥረት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ግብጽ የተለያዩ ሙከራዎችን በመጠቀም ላይ መሆኗን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት አገረቿ ጋር ማለትም ከሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት በመሆኑ ሙከራው የማይሳካ ህልም ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ የጎረቤት አገሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እያመሩ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሲመዘን አገራቱ ግብጽን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይንቀሳቀሳሉ ብለው እንደማያምኑም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ እንደመጣ የገለጹት አቶ ገዱ፤ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ በድንበር አካባቢ የሚነሳው ችግር ለዘመናት የቆየ በመሆኑ ችግሩን በዘለቂነት ለመፍታት ሁለቱ አገራት በጋራ እና በትብብር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተውን ሰሞነኛ ክስተት የግብጽ ሚዲያዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ በስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውንም አቶ ገዱ አብራርተዋል።

የግብጽ ሚዲያዎች ሃላይብ ትሪያንግል በመባል የሚታወቀውን የሱዳን መሬት ግብጽ በወረራ መያዟን በተመለከተ አንድም ቀን ሳይተነፍሱ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ እንደ ትልቅ አጀንዳ አንስተው ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው ያላቸውን ተዓማኒነት ትዝብት ውስጥ እንደሚከትም የተናገሩት።

ግብጾች ግድቡን ከእስራኤል ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀል መሆኑንም አቶ ገዱ በነበራቸው ቃለ ምልልስ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም