"ሂዌ" የተባለ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ለተቸገሩ አንድ ሺህ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
"ሂዌ" የተባለ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ለተቸገሩ አንድ ሺህ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
ደሴ፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን "ሂዌ" የተባለ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ በወገል ጤና ከተማ ለሚገኙ አንድ ሺህ አቅመ ደካሞች የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
"ሂዌ" የተባለው የመንገድ ሥራ ተቋራጭ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ጀንበሩ እንደገለጹት የመንገድ ሥራውን ከጀመሩ አንድ ዓመት ማስቆጠራቸውን ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ ከመንገድ ሥራው ጎን ለጎን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተለያዩ ልማቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ለችግር ለተጋለጡ አንድ ሺህ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉ 400 ኩንታል ዱቄትና 1 ሺህ 500 ሊትር ዘይት ሲሆን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ነው ብለዋል።
የተጀመሩትን የመንገድ ግንባታም በተያዘለት ጊዜ አጠናቀው ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዳዊት ቫይረሱ እስኪጠፋ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የደላንታ ወረዳ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አያሌው በሪሁን በበኩላቸው ኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ጫና ለመቀነስ ሁሉም የየድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።
መንገድ ተቋራጩ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የአቅመ ደካሞችን ችግር በጊዚያዊነት የሚያቃልል በመሆኑ ወረዳው ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል።
ደጋፉ በነፍስ ወከፍ 30 ኪሎ ግራም ዱቄትና አንድ ሊትር ዘይት ሲሆን ትርፉ 100 ኩንታል ዱቄትና 500 ሊትር ዘይት ለቀጣይ ጊዜ መጠባበቂያ መቀመጡን ተናግረዋል።
የመንገድ ግንባታ ድርጅቱ አካባቢውን በልማት እያገዘ መሆኑን ጠቁመው የመንገድ ሥራውን በወቅቱ አጠናቆ ለማስረከብም በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ድጋፍ ከተደረጋላቸው መካከል አቶ መኩሪያ ቸኮል በሰጡት አስተያየት ከኮሮና መከሰት በኋላ ስድስት ቤተሰቦችን ይዘው ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተው የተደረገላቸው ድጋፍ ጊዚያዊ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ገልጸዋል።
ወይዘሮ እመቤት ዳውድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ሥጋት በቤታቸው ለችግር ተጋልጠው እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው ሌሎች ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ድጋፉ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል።
"ሂዌ" የተባለው የመንገድ ሥራ ተቋራጭ በደቡብ ወሎ ዞን የተንታ መገንጠያ-ወገል ጤና -ኩርባ የአስፓልት መንገድ በመሥራት ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ አርሂቡ ኮምቦልቻ በጎ ድራጎት ማኅበር በኮምቦልቻ ከተማ ለሚኖሩ 500 አቅመ ደካሞች የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል።