በድሬዳዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር እየተሰራ ነው
ድሬዳዋ፣ ሰኔ 15/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተቀናጀ መንገድ በመተግበር የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።
የግብረ ኃይሉ አባል የሆነው በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ስለአዋጁ ክልከላዎችና መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በከተማው ተዘዋውረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ምህረቱ ቁምላቸው ክልከላዎች በማክበር ሂደት ሰፊ ክፍተት መኖሩን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ይህን ለማስተካከል ከማስተማሩ በተጓዳኝ የተዋቀረው የፀጥታ ግብረ ኃይልና የምርመራ ቡድን አስተማሪ እርምጃዎች እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስካሁንም የአዋጁ ክልከላዎችና ደንቦች በተላለፉ 22 ሰዎች ላይ እያንዳንዳቸው ከአንድ ወር እስከ አራት ዓመት እሥራትና ከብር ሁለት ሺህ እስከ 50 ሺህ እንዲቀጡ መወሰኑን ጠቅሰዋል።
ቅጣቱ የተላለፉባቸው ሰዎች ተሰባስበው ጫት ሲቅሙ፣ ሺሻ ሲያስጨሱ፣ መጠጥ ሲጠጡና ያልተገባ የቤት ኪራይ በመጨመር የተገኙ ናቸው።
ይህም ሆኖ ክልከላዎችን ባለማክበር የቫይረሱ ሥርጭት እየሰፋ ይገኛል ያሉት አቶ ምህረቱ ችግሩን ለማቃለል ሕግን የማስከበሩ ተግባር በተቀናጀ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን አዋጅና ደንብ በተገቢው መንገድ ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ ከድሬዳዋና ፌዴራል ፖሊስ ጋር በጥምረት መሥራቱን የተናገሩት ደግሞ የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ረድኤት ግርማ ናቸው።
ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በሕፃናትና ሴቶች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለመከላከል በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ አቶ ዘላለም ለታ በበኩላቸው አዋጁና ደንቡ የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ከኮሮና ለመታደግ የወጡ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ በማክበር ይህን ጊዜ በጥንቃቄ ማለፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች በከተማው ዋና ዋና የገበያ ማዕከላትና ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የግንዛቤ ትምህርት ከመስጠቱ ጎን ለጎን ደም ለግሰዋል።