ክፍለ ከተማው በህዳሴ ዋንጫ ገቢ ማሰባሰቢያ 29 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ክፍለ ከተማው በህዳሴ ዋንጫ ገቢ ማሰባሰቢያ 29 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተረከበው ዋንጫ 29 ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡን ገለጸ።
ዋንጫው በክፍለ ከተማው የነበረውን የ20 ቀናት ቆይታ አጠናቅቆ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስረክቧል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሳሁን በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በዋንጫው ገቢ በማሰባሰብ ''የላቀ'' ተሳትፎ አድርገዋል።
ዋንጫውን ከከተማ አስተዳደሩ ከመረከቡ በፊት በተነሳሽነት ሦስት ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡን አንስተዋል።
ክፍለ ከተማው በከተማዋ የመጀመሪያውን የዋንጫ ማዞርና የገቢ ማሰባሰብ ሥራ እንዲያከናውን የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም ከባለኃብቶች፣ከመንግሥት ሠራተኞች፣ከሴቶችና ከወጣቶች ማህበራትና ከነዋሪዎች 29 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ከክፍለ ከተማው 32 ሚሊዮን ብር ገቢ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ አካላት 15 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ በከተማዋ በተስፋፋበትና ሕዝቡ ትኩረቱን ለቫይረሱ በሰጠበት ወቅት በተለይም ገቢያቸው የተቀዛቀዘ ነጋዴዎች ለግድቡ ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር ገልጸዋል።
ይህም ''የግድቡ ግንባታ በሕዝቡ ውስጥ የእኔነት ስሜትን የፈጠረ እንደሆነ ያመላከተ ነው'' ብለዋል።
የአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲ በበኩላቸው ''በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከግብጽ በኩል የራስ ወዳድነት ፍላጎት እየተንጸባረቀ ባለበት በዚህ ወቅት ለግንባታው ይህን መሰል ርብርብ መደረጉ የእንችለዋለን ስሜት አሁንም እንዳለ የሚያመላክት ነው''።
በተጨማሪም ግድቡን በሚመለከት እየወጡ ያሉ መረጃዎች በሕዝቡ ላይ ቁጭትንና የባለመብትነት ስሜትን በመፍጠራቸው ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ማጠናከሩን ገልጸዋል።
ክፍለ ከተማው ኮቪድ-19 ላይ የሚከናወኑ የመከላከልና የመደጋገፍ ሥራዎችን በተጓዳኝ ለግንባታው ገቢ በማሰባሰብ ያስመዘገበው ውጤትና ለተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን ችረዋል።
በዋንጫው ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ በገቢ አሰባሰብ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ወረዳዎች የእውቅና ሰርተፊኬትና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
የከተማው አስተዳደር በዋንጫው 100 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ማቀዱ ተገልጿል።