ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፍጆታ ምርቶችን ከውጭ ማስገባታቸው ለዋጋ ማረጋጋት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፍጆታ ምርቶችን ከውጭ ማስገባታቸው ለዋጋ ማረጋጋት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ ሂሳብ ደብተር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የፍጆታ ምርቶችን ከውጭ ማስገባታቸው ገበያውን እያረጋጋ መሆኑን የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አስታወቁ።
መንግሥት የኮቪድ- 19 መከሰትን ተከትሎ የአቅርቦት ክፍተትና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት የዲያስፖራ አካውንት ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ልምድ ላላቸው ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል።
ጨረታው በአንድ በኩል በአገሪቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የፍጆታ ምርት ክፍተት መሙላትና በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስታገስ በተወሰነው መሠረት እየተካሄደ ነው።
በዚህ መሠረት የዲያስፖራ ሂሳብ ደብተር ኖሯቸው መንግሥት እጥረት አለ ብሎ ባመነባቸው እንደ ሩዝ፣ ዘይት፣ ስኳርና መሰል ምርቶችን ለማስገባት መስፈርቱን ያሟሉ ስድስት አቅራቢዎች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እያቀረቡ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሸቴ አስፋው ለኢዜአ ተናግረዋል።
በገበያ ማረጋጋቱ ላይ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁት የውጭ ኩባንያዎች እስካሁን የተመዘገቡት 38 ኩባንያዎች ተመዝግበው ምዝገባቸው በመስፈርቱ መሠረት እየተጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብና በሌሎች መስፈርት ላይ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ በሌሎች ጨረታዎች እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
መስፈርቱን የሚያሟሉት የውጭ ኩባንያዎች በቅርቡ አቅርቦት እንደሚጀምሩም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ እንደተከሰተ ታይቶ የነበረው የዋጋ ጭማሪ መንግሥት ባቋቋመው ግብረ ኃይል ቁጥጥር ባይደረግበትና በአቅርቦቱ ላይም ሥራ ባይሰራ ኖሮ፤ ኅብረተሰቡ ጫና ውስጥ ይገባ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይ በገበያ ላይ ጣልቃ በመግባት የዋጋ ጭማሪን የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ደላሎችንና ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ የሕዝቡ ተሳትፎ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
በንግድ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ጥፋት የፈጸሙ ከ64 ሺህ በላይ አጥፊዎች ሕጋዊና አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን የገለጹት አቶ እሸቴ፤ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።