ቀጥታ፡

የብሮድካስት ባለስልጣን ለሶስት የሬድዮ ጣብያዎች ፈቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሶስት አዳዲስ የሬድዮ ጣብያዎች ፈቃድ ሰጠ።

ፈቃድ ያገኙት ሬድዮ ጣብያዎቹ ኢትዮ ዋርካ መልቲ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን፣ ትርታ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና አዲስ ኦንላይን የሚዲያና የግብይት ስራዎች ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የተለያየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን እንዲበራከቱ ይፈለጋል።

ይህም በተለይ ህብረተሰቡ የመረጃ አማራጮችን ከማስፋቱ ባሻገር በተለያዩ አቅጣጫዎች ከጣቢያዎቹ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ትልቅ ደርሻ አለው ብለዋል።

ፈቃድ የተሰጣቸው ጣቢያዎች በተሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ራሳቸውን ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በማድረግም አገራዊ፣ ህዝባዊና ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ባለስልጣኑ የሚዲያ ልማትን ማሳደግና ማስፋፋት ላይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን ከሰተጣቸው ሃላፊነት ውጪ በመሰሩና ህዝብን ከህዝብ እና ከመንግስት ጋር የሚያጋጩ ስራዎችን በሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ72 በላይ የማህበረሰብ፣ የግል (የንግድ) እና የህዝብ የሬድዮ ጣብያዎች አሉ።

አሁን ላይ 37 የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሉም ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም