ደን የሚመነጥሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ህዳሴ ግድብ ማጓጓዝ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ደን የሚመነጥሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ህዳሴ ግድብ ማጓጓዝ ተጀመረ
አሶሳ፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጫ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ በመጪው እሁድ ምንጣሮውን ለመጀመር ኢንተርፕራይዞች ወደ ስፍራው እየገቡ መሆናቸው ተገለፀ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው የግድቡ ውሃ የሚተኛበትን አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደን ምንጣሮ ለማከናወን ባለፈው ሐሙስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦታ ርክክብ አድርጓል፡፡
ስራውን ለማፋጠን ኤጀንሲው ከአሁን በፊት ምንጣሮውን ለማካሔድ ውል የገቡት የኢንተርፕራይዞች ቁጥር ከ45 ወደ 61 ከፍ እንዲሉ ማድረጉን አስታውቋል።
በኢንተርፕራይዞቹ ታቅፈው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ቁጥር ከሁለት ሺህ በላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለምንጣሮ ስራው ከተያዘው አጠቃላይ በጀት ስድስት ሚሊዮን ብር ለስራ ማስኬጃ እንዲሆናቸው ወደ ኢንተርፕራይዞቹ የባንክ ሒሳብ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከትናንት ጀምሮ በኢንተርፕራይዞቹ የሚመነጠረውን መሬት በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ተሸንሽኖ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ በሽር ጠቁመዋል፡፡
ለእያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ እንደየአቅማቸው ከሰባት ሄክታር እስከ 18 ሄክታር የሚደርስ የሚመነጠር ደን ያለው መሬት ይደርሳቸዋል ብለዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ የምንጣሮ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ስራውን ለመጀመር ከዛሬ ጀምሮ ወደ ህዳሴው ግድብ አካባቢ እየገቡ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው የምንጣሮ ስራው በመጪው ሐሙስ በይፋ እንደሚጀመር አስረድተዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ አጠናቅቀው እንደሚያስረክቡ በውል ስምምነት ላይ መጠቀሱን ከአቶ በሽር ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።
የህዳሴው ግድብ በተለይም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ ትኩረት የሚከተለው መሆኑን የክልሉ መንግስት በሚገባ ይረዳል ያሉት አቶ በሽር የምንጣሮ ስራውን የሚከታተል በክልሉ መንግስት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡
የኮሚቴው ዋነኛ ተግባር የምንጣሮ ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በየዕለቱ ክትትል ማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም ምንጣሮውን የሚያካሂዱ ወጣቶች ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ራሳቸውን ከወባና ሌሎች በሽታዎች እንዲጠበቁ ቁሳቁስ የሚያቀርብ የጤናና የጸጥታ ቡድን በኮሚቴው እንደተደራጀ አስረድተዋል፡፡
ለደን ምንጣሮ ስራው የሚውል አጠቃላይ በጀት 32 ነጥብ 1 ብር እንደሆነም ከዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል፡፡