አካል ጉዳተኞችን ከኮቪድ-19 ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞችን ከኮቪድ-19 ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
የአካል ጉዳተኞችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከመንግስት፤ከባለድርሻ አካላት እና ከማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
መስማት የተሳናቸው አካል ጉዳተኛ የሆኑት ወይዘሮ ትግስት አለማየሁ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተሰራ ያለው ስራ በዝቅተኛ ኖሮ ደረጃ ላይ ላለው አካል ጉዳተኛ መረጃዎች ተደራሽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ትግስት አክለውም የሚደረገው ድጋፍም ካለው የአካል ጉዳተኞች ተደራራቢ ችግር አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያወሱት፡፡
እስካሁን ባለው በመንግስትም ሆነ በአካል ጉዳተኞች ማህበር ፌዴሬሽን በኩል የተለያዩ
ድጋፎች እተደረገላት እንደሆነ የገለጸቸው ደግሞ ማየት የተሳናት አካል ጉዳተኛ ወይዘሮ ሰላም በላይ ነች፡፡
″በራሴ በኩል ቫይረሱን ለመከላከል ማድረግ ያለብኝን ጥንቃቄዎች በሚገባ አደርጋለው ፤ነገር ግን አሁንም እስከታች ድረስ ድጋፉ እና መረጃው ተደራሽ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አካል ጉዳተኛ የሆኑት አቶ ሲሳይ ተሰማ እንዳለው ለሚደረገው ርብርብ አመሥግነዋል።
በድጋፍ ብቻ የሚተዳደሩ አካል ጉዳተኞች በኮሮና ምክንያት የሀይማኖት ተቋማትና ሰዎች የሚበዙባቸው አካባቢዎች በመዘጋታቸው ከህበረተሰቡ የሚያገኙትን አሁን ላይ ማግኘት ስለማይችሉ በልዩ ሁኔታ ድጋፉ ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአካል ጉዳተኞች ያነሷቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ የሚያብራሩት የፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር አቶ አባይነህ የአካል ጉዳተኞች በቫይረሱ እንዳይጠቁ ዊልቸር እና መሰል የሚገለገሉባቸው ቁሶችን የማጽዳት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ደረጃ ከ300 በላይ መስማት እና ማየት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ያስረዱት አቶ አባይነህ የተለየ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱ በሀገሪቱ መግባቱ ከታወቀ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንጽህና
መጠበቂያና የምግብ እርዳታ እንዲሁም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2 ነጥብ
1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ሌሎችም በጎ አድራጊ ድርጆቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባደረጉት የመረዳዳት ጥሪን ተከትሎ በርካታ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁንም እርዳታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በሀገሪቱ ከ18 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች በመኖራቸው የመረጃ እና መሰል ችግሮች
ስላሉባቸው ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ዳይሬክተሩ
አሳስበዋል፡፡