ግብጽ የግድቡን ጉዳይን ወደ ተመድ መውሰዷ አግባብነት የለውም - ደቡብ ሱዳን - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ የግድቡን ጉዳይን ወደ ተመድ መውሰዷ አግባብነት የለውም - ደቡብ ሱዳን
ሰኔ 16/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ግብጽ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት መውሰዷ አግባብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ደንግ አስታወቁ።
ጉዳዩ በአፍሪካ ማለቅ ሲገባው ወደ ኒውዮርክ መውሰዱ ትክክል እንዳልሆነም ምክትል አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
ምክትል አምባሳደሩ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ አበባም ሆነ ካይሮ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
አፍሪካ ህብረትን አልፎ ወደ ተባበሩት መንግስታት መውሰድ አግባብ አለመሆኑን በማከል፡፡
ኢትዮጵያና ግብጽን ያላስማማው ጉዳይ በአፍሪካ ደረጃ ሳይታይ ወደሌላ የዉጭ አካል መወሰዱ ተገቢነት የሌለውና የአፍሪካን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚጻረር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ደንግ ኮንግ በደቡብ ሱዳን ውስጥ አንድም የግብጽ ወታደር አለመኖሩንና ምንም አይነት መሬት ለየትኛውም ሀገር አለመሰጠቱንም አረጋግጠዋል፡፡በደቡብ ሱዳን በኩል አድርጎ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል የትኛውም ሃይል በሀገራቸው ተቀባይነት እንደሌለው ያነሱት አምባሳደር ዴቪድ ደንግ "ኢትዮጵያ ጎረቤታችን ብቻ ሳትሆን ሁሉም ነገራችን ናት" ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ብቻ አይደለም የምንጋራው ያሉት ዲፕሎማቱ “ህዝባችን ፣ባህላችን፣ ቋንቋችን እና ሌሎች ነገሮቻችንም የተያያዙና የተሳሰሩ ናቸው” ብለዋል፡፡
ምክትል አምባሳደሩ አክለውም “በደቡብ ሱዳን በኩል ኢትዮጵያን እጎዳለሁ ብሎ ያሰበ ሃይል በቅድሚያ የሚጣላው ከደቡብ ሱዳን ጋር ነው” ሲሉ መናገራቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡