ወልቂጤ ከተማ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ወልቂጤ ከተማ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ ሐምሌ 2/2010 ወልቂጤ ከተማ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆኗል። ወልቂጤ የሊጉ አሸናፊ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ትናንት በሃዋሳ በተደረገ የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 55 ለ 47 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ሃዋሳ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች ያላቸው ነጥብ 27 ቢሆንም ወልቂጤ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ጋር እርስ በእርስ ሲጫወት ያስቆጠረው ቅርጫት የተሻለ በመሆኑ የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል። ሃዋሳ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት በ22 ነጥብ ሶስተኛ ወጥቷል። ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት ቡድኖች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ዘመዴ በቀለ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ፣ የሃዋሳ ከተማው ፓኜ ኦባላ የሊጉ ኮከብ ተጫዋችና ቢኒያም ዳዊት የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ዳኛ በመሆን ተመርጠው የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ፓኜ ኦባላ በውድድር ዓመቱ 24 ጊዜ ሶስት ነጥብ ቅርጫት በማስቆጠር ኮከብ የ3 ነጥብ የቅርጫት ኳስ አስቆጣሪ ሆኖ ተመርጧል። ወልቂጤ ከተማ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።