ለክፍያ መንገድ ተጠቃሚዎች የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለክፍያ መንገድ ተጠቃሚዎች የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ለክፍያ መንገድ ተጠቃሚዎች የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ እየገነባሁ ነው አለ።
እስካሁን በኢትዮጵያ ሁለት የክፍያ መንገዶች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ለመንገዱ ተጠቃሚዎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ጣቢያዎች የላቸውም።
ስለሆነም አገልግሎቱን የሚመጥን የነዳጅ ማደያ፣ የሆቴልና የቴክኒክ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት መገንባት መጀመሩ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ አዳማ የክፍያ መንገድ ላይ ግራና ቀኝ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ ግንባታ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ የመገንባት ሥራ ተጀምሯል።
በኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የመንገድና መንገድ ሀብት ጥገና እና የትራፊክ ደህንነት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኪዳኔ ይፍሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቹ በተለይም ለረጅም ርቀት ጉዞ አሽከርካሪዎች ማረፊያነት ወሳኝ ናቸው።
እንደ አቶ ኪዳኔ፤ በአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ ላይ የተጀመረው ግንባታ ለተጠቃሚዎች ሁለገብ አገልግሎት በመስጠት አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይፈታል።
የኢንተርፕራይዙ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ሮቤል አያሌው በበኩላቸው ጣቢያዎቹ ለተገልጋዮቹ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጣቢያዎቹ መገንባት አሽከርካሪዎች በጉዞ ላይ የሚያጋጥማቸውን የቴክኒክ ችግሮች ለመፍታት እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
መንገዱ በቀጣይ ለሚሠሩ የክፍያ መንዶች ሥራ ተሞክሮ እየተወሰደበት እንደሆነም አመልክተዋል።
በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ለሚከናወነው የተቀናጀ አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ግንባታ ማስፈጸሚያ 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን አቶ ኪዳኔ ገልጸዋል።
ጣቢያዎቹ ለሚገነቡበት አካባቢ ማህበረሰብ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ታስቦ የዲዛይን ዝግጅት ተደርጎ ወደ ግንባታ መገባቱንም አስረድተዋል።
የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚቀጥለው አመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ አዳማ እና የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን የሞጆ ሐዋሳ የክፍያ መንገድ በግንባታ ላይ ይገኛል።