ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ለተሰዉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች መታሰቢያ ችግኝ ተተከለ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ለተሰዉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች መታሰቢያ ችግኝ ተተከለ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 15/2012 ( ኢዜአ) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳርና በአዲስ አበባ ግድያ የተፈፀመባቸውን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መታሰቢያ ችግኝ ተተክሏል።
በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተካሄደው የመታሰቢያ ችግኝ ተከላ የከተማዋ ምክንትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኤርትራ ተወላጆችና በጎ ፈቃደኞችም ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የችግኝ ተከላው ለአገራቸው እድገት ሲታገሉ ለተሰዉት የመከላከያና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች መታሰቢያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት አለመግባባቶችን በሃሳብ በመፍታት በአንድነት መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለአገራቸው ብልጽግና ሲታገሉ የነበሩና መስዋዕት የሆኑ ከፍተኛ አመራሮችን ራዕይ እውን ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
አቶ ተስፋዬ በንግግራቸው አመራሮቹ ቢሰዉም ራዕያቸው ህያው ነው ሲታወሱ ይኖራሉ ብለዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ካሳሁን በክፍለ ከተማው ሊተከል ከታቀደው 1 ሚሊዮን ችግኝ ለአመራሮቹ መታሰቢያ እንዲሆን ዛሬ 1 ሺህ 200 መተከሉን ገልጸዋል።
ይህም አመራሮቹ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ያከናወኗቸውን መልካም ተግባራት የሚያስታውስ ይሆናል ብለዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፈው ኤርትራዊ ወጣት ዮናስ ተመስገን በ5 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ዘመቻ አሻራውን በማሳረፉ ዕድለኝነቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የተሰዉበትን ቀን ለማሰብ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መሆኑም የተለየ እንደሚያደርገው ገልጾ የመገዳደልን አስከፊነትን ከወንድማማች የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች መማር ይኖርብናል ብሏል።
ወይዘሮ አክበረት አብርሃም በበኩላቸው የተከሉትን ችግኝ በቀጣይም በመንከባከብ ለአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የቀድሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንና ጓዶቻቸው እንዲሁም የቀድሞው የጦር ኃይሎች አዛዥ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን መሰዋታቸው ይታወሳል።
በችግኝ ተከላው ከ300 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።