ቀጥታ፡

ለይዞታቸው የተተመነላቸው ካሳ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ያላገናዘበ መሆኑን በሰቆጣ ከተማ የልማት ተነሺዎች ቅሬታቸው ገለጹ

ሰቆጣ ሐምሌ 1/2010 ለመኖሪያ ቤታቸውና ለመሬት ይዞታቸው የተተመነላቸው የካሳ ግምት የወቅቱን የገበያ ዋጋ ያላገናዘበ መሆኑን በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ የልማት ተነሺዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ የብልባላ ሰቆጣ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ከይዞታቸው የሚለቁት እነዚህ 140 የልማት ተነሺዎች ቅሬታቸውን በየደረጃው ለሚገኙ የአስተዳደር አካላት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከልማት ተነሺዎች መካከል የከተማዋ ቀበሌ ሁለት ነዋሪ  አቶ አብዱቃድር ካሳየ ለኢዜአ እንዳሉት እየተሰራ የለውን የመንገድ ፕሮጀክት ለአካባቢው  ያለውን አስተዋጽኦ በማመን ከመኖሪያ ቤታቸው ለመነሳት ፍላጎታቸው ቢሆንም የተሰራው የካሳ ግምት ፍትሃዊ አይደለም፡፡ የቦታ መለካት ስራው  ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ባለመገመቱ ተመሳሳይ ለሆኑ ቤቶች የተለያየ የዋጋ ተመን እንደወጣላቸው የተናገሩት አቶ አብዱቃድር ይህም ተገቢነት እንደሌላውና አሁን ያለውን የቤት መስሪያ ዋጋ ያገናዘበ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በተለይም የካሳ ገማች ኮሚቴው የቦታ ግምት ስራ ከማከናወኑ በፊት ለልማት ተነሺዎች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲዘጋጁ አለመደረጉንም ጠቁመዋል። ሌላው የልማት ተነሺ  ኢንስፔክተር መብራት አሸብር በበኩላቸው "የቤት የካሳ ግምት ሲወጣ የቤት ኪራይንና የንብረት ማንሻ ገንዘብን ክፍያ ታሳቢ ያላደረገ ሂሳብ እንዲወጣ ተደርጓል" ብለዋል፡፡ የልማት ተነሺዎች ተመጣጣኝ  የሆነ መሰረተ ልማት የተሟላበት የመስሪያ ቦታ እንዳልተዘጋጀላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የአስፓልት ካሳ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙላት በርሄ "ከጥቅምት 2010 ዓ.ም ጀምሮ 140 ግለሰቦች መጀመሪያ በተሰራው ካሳ ግመታ እንዲስተካከልላቸው ቅሬታቸውን አስገብተዋል" ብለዋል፡፡ ገማች ኮሚቴው በከተማው የልማት ተነሺዎችን የካሳ ግምት ከሰራ በኋላ  የሚገባቸውን ንብረቶች እንዲካተትላቸው ግለሰቦቹ ሲጠይቁ በድጋሜ የካሳ ሂሳብ መውጣት መቻሉ በአጣሪ ኮሚቴው ችግሮች መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም በካሳ ግምቱ ክፍተት ፈጥረዋል የተባሉ ግለሰቦች ከኃላፊነት እንዲነሱ እና የእገዳ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታው ፈጠነ በበኩላቸው "የልማት ተነሺዎችን  ቅሬታ ለመፍታት አዋጅና መመሪያን መሰረት ያደረገ  የካሳ ግምት ዳግም ይሰራል" ብለዋል፡፡ የካሳ ትመና ቅሬታን ለመፍታት ከህዝቡና ከባለሙያዎች የተወጣጣ  አዲስ ገማች ኮሚቴ እንደሚዋቀር ጠቅሰው የልማት ተነሺዎችም የቤት ግምት የወቅቱን የገበያ ዋጋ ባገናዘበ መልኩ አዲስ የግምት ተመን እንደሚወጣ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሰሜን ሪጅን የፋይናንስና መንገድ ማኔጅመንት ቡድን መሪ አቶ ነብዩ ተስፋዬ  እንዳሉት ደግሞ  ባለስልጣኑ ክልሉ ባወጣው የከተሞች ደረጃ መሰረት የካሳ ትመናው ይሰራል፡፡ የልማት ተነሺዎች የቤት ኪራይና ንብረት ማስነሻ ገንዘብ ተመን ጥያቄ  በካሳ አከፋፈል አዋጅ መሰረት እንደሚስተናገድ አመልክተው፤ መንገዱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን መወጣት አንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የብልባላ ሰቆጣ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 98 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም