ኅብረተሰቡ በጣና በለስ እና አካባቢያዊ ጸጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በትብብር ይሰራል--- አቶ ተመሥገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረተሰቡ በጣና በለስ እና አካባቢያዊ ጸጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በትብብር ይሰራል--- አቶ ተመሥገን ጥሩነህ
ሰኔ 14/2012(ኢዜአ) ኅብረተሰቡ በጣና በለስ እና አካባቢው ጸጋዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ለ30 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የጣና በለስ አየር ማረፊያ ዛሬ የሙከራ በረራ ተደርጎበታል።
የጣና በለስ አየር ማረፊያን በአዲስ መልክ ለማስጀመር እድሳት ሲደረግለት ሰንብቷል።
እድሳቱ የተከናወነውም በጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እና በኢትዮዽያዊው ባለሃብት በአቶ ወርቁ አይተነው አማካኝነት እንደሆነ ታውቋል።
ይህን ተከትሎም ዛሬ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም የሙከራ በረራ ተደርጎበታል።
በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው እና ሌሎች የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሀ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ኅብረተሰቡ በጣና በለስ እና አካባቢው ጸጋዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ታድሶ ለሥራ ዝግጁ መደረጉ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው እንዲሄዱና እንዲያለሙ ለማድረግ ምቹ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
አቶ ወርቁ አይተነው ለሥራው አስተዋጽዖ በማድረጋቸውም ርዕሰ መሥተዳድሩ አመሥግነዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰንም ባለሀብቱ ለሁለቱ ክልሎች የልማት አጋር መሆናቸውን በመግለጽ አመሥግነዋል።
በቀጣይ መደበኛ በረራ እንዲጀመርበት የክልሉ መንግሥት ጥያቄዎቹን አደራጅቶ በማቅረብ ክትትል እንደሚያደርግም አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል።
የደብሊው ኤ የዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው በአካባቢው ለኢንቨስትመንት ለመሠማራት ለተሰጣቸው በጎ ምላሽ አመሥግነዋል።
በቀጣይም ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ልማት በትኩረት እንደሚሠሩ መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።
የጣና በለስ አየር ማረፊያ ለ 30 አመታት አገልገሎት ሳይሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።