ቀጥታ፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ውይይት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲገኙ ጥሪ ተላለፈ

አዲስ አበባ ሀምሌ1/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲገኙ አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪ አስተላለፈ። "ግንቡን እናፈርሳለን ድልድዩን እንገነባለን" በሚል መሪ ሐሳብ ሐምሌ 21 እና 22 ቀን 2010ዓ.ም በዋሽንግተንና በሎሳንጀለስ ከተሞች የሚደረገውን መድረክ አስመልክተው የመድረኩ አስተባበሪዎች በአሜሪካ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት በውይይቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአኗኗር ሁኔታውና በፖለቲካ አመለካከቱ ሳይገደብ በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል። ግንቡን አፍርሶ ድልድዩን ለመገንባት ውይይቱ በሰሜን አሜሪካ ቢደረግም በተለያዩ አገራት የሚኖሩና መገኘት ለማይችሉትም ጭምር  የመልካም ተግባር ምልክት መጀመሪያ ሞዴል ስለሆነ ሁሉም በውይይቱ በመገኘት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የውይይት መድረኩ ዲያስፖራው የአገሩ እሴትና ሃሴት መሆኑን እንዲሁም መንግስት የሚመራት አገር ለዲያስፖራው አገሩና ቤቱ መሆኗን የሚገለጽበትና የግንኙነት ድልድይ የሚዘረጋበት ነው በማለት አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልባዊ እምነትና የአገሪቷ ጥሪ የሆነው ይህ የውይይት መድረክ ሲካሄድ በኢትዮጵያ የ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ በይዘቱና በመጠኑ የተለየ ነው። የውይይት መድረኩ ልባዊ ይቅርታን ለመጀመር ብሩህ ተስፋ የተሰነቀበት መሆኑን ጠቁመው ይህም ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን፣ መተማመንና መቀራረብ እንዲጎለብት፣ አርቆ አሳቢነትና የሃሳብ ልእልና ባህል እንዲመጣ "የመጀመሪያው ምዕራፍና በር ከፋች መድረክ ነው" ሲሉ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ኤምባሲው  በፍቅርና በአንድነት ተሳስቦና ተቀራርቦ በመስራት ብዙ ለውጥ እንደመጣ ጠቅሰዋል። እስካሁን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት በጉጉት ከመጠበቅ ባለፈ ኃላፊነት በመውሰድ በርካታ ገንዘብና ጊዜ በማፍሰስ ሰልፍ በመውጣትና በማስተባበር ላሳዩት ተግባር አምባሳደር ካሳ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ግንቡን አፍርሶ ድልድይ ለመገንባት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ተባብሮ በጥንካሬ እንዲሰራ ጠይቀዋል። የኮሚቴው ጸሓፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የውይይት መድረኩ "የኢትዮጵያ የሰርግ ቀን" መሆኑን ጠቅሰው፤ በመድረኩ የተለያዩ እምነት፣ ፆታ፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ከዚህ በፊት ተያይተው የማይተዋወቁ ሰዎች ለአንድ ዓላማ የሚሰለፉበት ነው ብለዋል። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጠሪና መሪ ሳያስፈልገው የአገሬ ሰላምና አንድነት ያገባኛል በሚል መንፈስ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራዎች ያሏት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት በሰሜን አሜሪካ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም