ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በአንድነት ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተፎካካሪ የፓርቲ አመራሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በአንድነት ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተፎካካሪ የፓርቲ አመራሮች ተናገሩ
ጋምቤላ፣ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) የፖለቲካ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው የህዝብንና ሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በአንድነት ተባብሮ መስራት እንደሚገባ በጋምቤላ ክልል ሁለት ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ዙሪያ መንግስት የያዘውን አቋም እንደሚደግፉም የፓርቲ አመራሮቹ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትየጵያ ከራሱ መሬት የሚፈልቀውን የአባይን ውሃ የማንንም ፍቃድ ሳትጠይቅ የመጠቀም መብት እያለት ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ጋር በጋራ ለመገልገል ወደ ድርድር መግባቱ አስተዋይና ሆደ ሰፊ መሆኗን እንደሚያመለክት አስታውቀዋል።
አመራሮቹ እንዳሉት አሁን ላይ ማንኛውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ከመንግስት ጎን በመሆን የህዝብንና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በአንድነት ተባብሮ መስራት ይጠበቅበታል።
የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን/ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን በሰጡት አስተያየተ ለህዝቡንና ሀገሪቱ እድገትትልቅ ተስፋ ለተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ስኬት ሁሉም በጋራ መረባረብ እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይም አሁን ላይ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እውን እንዳይሆን እየሰሩ ላሉ የውጭ ጠላቶች ክፍታት ላለመፍጠር ሁሉም ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ በአንድነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
አቶ ፒተር ኢትየጵያዊያን አንድ ከሆኑ ማነኛውም ጠላት አሳፍረው እንደሚመልሱ የዓለም ህዝብ ያውቃል፤ በዚህ ጊዜ መሀል ሰፋሪ መሆን አያስፈልገም ሲሉ ገልጸዋል።
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚደራጀው ለሀገርና ህዝብ ጥቅምና መብት መከበር እስከ ሆነ ድርስ ፓርቲዎች ያለ ልዩነት ከመንግስት ጎን በመሆን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ሊሰሩ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የጋህነን አመራር አቶ ተዘራ ኃይለማሪታም ናቸው።
ኢትየጰያ ከራሷ የሚመነጨው የአባይ ወንዝን በፍትሃዊነት ለመጠቀም ህዝቦቿን በማስተባበር እያደረገች ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ በግብጽ በኩል እየቀረበ ያለው ሃሳብ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ኢትየጵያ ከራሱ መሬት የሚፈልቀውን የአባይን ውሃ የማንንም ፍቃድ ሳትጠይቅ የመጠቀም መብት እያለት ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ጋር በጋራ ለመገልገል ወደ ድርድር መግባቱ አስተዋይና ሆደ ሰፊ መሆኗን ያመለክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራር አቶ ኦኬሎ አኳይ በበኩላቸው ኢዜማ ለሀገር ሰላም፣ እድገትና ለህዝብ ጥቅም መከበር አበክሮም የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠንና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለጀመረው ለታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ኢዜማ በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።
ሀገርና ህዝብ ሲኖር ነው ፓርቲ የሚኖረው ያሉት አቶ ኦኬሎ አሁን ላይ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመመከት ፓርቲዎቹ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።