ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ቀለበታማ የፀሃይ ግርዶሽ ታይቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14 / 2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ከ50 ደቂቃዎች ጀምሮ ቀለበታማ የፀሃይ ግርዶሽ ታይቷል።

ግርዶሹ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ላልይበላን ጨምሮ በሞጣ፣ ደብረታቦር፣ አላማጣ፣ ጋይንት እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎችም ታይቷል።

በተለይ በላልይበላ  በርካታ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በሰፍራው ተገኝተው የተከታተሉት ሲሆን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ፀሐይ እሳታማ ቀለበት ሰርታ ታይታለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ6 ሠዓታት የሚቆየው ይህ ግርዶሽ ከኮንጎ ነው መነሻውን ያደረገው።

ቀለበታማ የፀሃይ ግርዶሹ መነሻውን ኮንጎ በማድረግ በማዕከላዊ አፍሪካ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ኤርትራ ተስተውሏል። 

እንደ አልጀዚራ ዘገባ ከሆነ በመካከለኛ ምስራቅ አገራት እንዲሁም ህንድና ቻይናም ተመሳሳይ ክስተት የነበረ ሲሆን በዓለማችን ለ6 ሰዓታት ቆይቷል።

የፀሃይ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ ፣ ፀሐይና በምድር ትይዩ በሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ጨረቃ ከመሬት በሚኖራት የርቀት ምጣኔ መሰረትም የግርዶሹ አይነት የሚወሰን ይሆናል።

ይህንንም ተከትሎም በዛሬው እለት ቀለበታማ የፀሃይ ግርዶሽ ሊከሰት ችሏል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያመለክተው ቀለበታማ የፀሃይ ግርዶሽ ከ18 ዓመታት በኋላ ሲስተዋል ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ደግሞ ከ146 ዓመታት በኋላ ይከሰታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም