ቀጥታ፡

ግብፅ የህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም ዓባይን እኔ ብቻ ልጠቀምበት የሚል ነው - የታሪክ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም ዓባይን እኔ ብቻ ተጠቅሜ ልበልጽግ ከሚል ሚዛናዊነት የጎደለው እሳቤ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን አስታወቁ።

ምሁራኑ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝንና ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አቋሟን በስፋት ማስረዳት ይኖርባታልም ብለዋል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ዶክተር ሰይድ አህመድ እንደሚሉት በዚህ ዘመን የግብፅ "የእኔ ብቻ" ምኞት አክትሞለታል።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የግብፅ መሪዎች ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ በመምጣት ግዛት ያስፋፉት የዓባይን ውኃ ለመቆጣጣር እንደነበር ያስታወሳሉ።

የግብፅ እኔ ብቻ ልጠቀም አቋም በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባችውን የአስዋን ግድብና ታላቁ ሰው ሰራሽ የናስር ሀይቅ የሚጠቀስ መሆኑንም ዶከተር ሰይድ ተናግረዋል።

ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1929 ከእንግሊዝ ጋር እንዲሁም በ1959 ከሱዳን ጋር የፈረሙትና ኢትዮጵያን ያላሳተፈ የቅኝ ግዛት ሥምምነት የግብፅን ለብቻ የመጠቀም ፍላጎት በግልፅ ያሳየም ነው።

ሱዳን እ.ኤ.አ በ1929 በተፈረመው ሥምምነት መነሻ ፍትሐዊ ተጠቃሚ አይደለሁም ብላ በመቃወሟ ግብፅ እ.ኤ.አ በ1958 በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት እንዲደረግ ድጋፍ አድርጋ የ1959 ሥምምነት ሱዳን እንድትፈርም ማስገደዷን አውስተዋል።

የቅኝ ግዛት ውሎቹ የዓባይ ውኃ ምንጭ የሆነችውን የኢትዮጵያ መብት ያልጠበቀና ያላማከለ በመሆኑንም ነው ዶክተር ሰይድ ያስረዱት።

ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ፣ የምታሳየው አቋም ከጥንት ጀምሮ ግብፅ ከነበራት የተሳሳተና ኢ-ሚዛናዊ እሳቤ የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያላት አቋም በፍትሐዊነት የመጠቀምና የማደግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም አቋሟን አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኪተቦ አብዲዮ ግብፅ የአባይ ወንዝን ለብቻ ልጠቀም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ከፈርኦኖች ታሪክ ጊዜ የነበረ ነው ብለዋል።

እ.ኤ.አ. ከ1505 እስከ 1549 ግብፅን የመራውና ወደ ዘመናዊ ሥልጣኔ እንደመጣች የሚናገረው መሐመድ ዓሊ የዓባይ ወንዝ የጎርፍ አደጋ እንዳያደርስና ሌሎች ጠቀሜታዎችን ግብፅ እንድታገኝ መከላከያ (ባራጅ) ሰርተው እንደነበር አውስተዋል።

ይህም ቀጥሎ በ1990ዎቹ ግብፅ የአስዋን ግድብን በእንግሊዝና በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ድጋፍ ስትገነባ የተፋሰሱ አገራት ይሁንታ አልነበረውም።

የግብፅ አቋም ኢትዮጵያና ሌሎች የተፋሰስ አገራት ያላቸውን የውኃ ሀብት ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝና ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያላትን መብትና አቋም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት ይጠበቅባታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በዲፕሎማሲው ረገድ የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም