ቀጥታ፡

ፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሕን ለማረጋገጥና ሰላም ለማስፈን ከመንግሥት ጋር በትብብር መሥራት አለባቸው - ጠበቃ ወንድሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ፍትሕን ለማረጋገጥና ሰላም ለማስፈን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ከገዥው ፓርቲና መንግሥት መተባበር እንደሚገባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ ተናገሩ።

ገዥው ፓርቲና መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች "እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን" ከሚል ራስ ወዳድ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ "ለውጥ" መጣ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በሽብር ተከሰው ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉ ግለሰቦችና ፓርቲዎችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በአገራቸው መኖር ጀምረዋል።

የደቦ ፍርድ ንጹሐንን ለሞትና እንግልት እየዳረገ ቢሆንም በአገር ውስጥ እስረኞች ተፈተዋል፤ መንግሥት በዜጎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀርቷል ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት ለውጥ ሲከሰት ለውጡ የሚመጣላቸው ብዙሃንና ለውጡ የሚመጣባቸው ቡድኖች መኖራቸው አይቀርም።

"በኢትዮጵያም የተከሰተው ይኸው ነው። ለዓመታት በንጹሐን ላይ ያለ በደላቸው የመከራ ዶፍ ሲያወርዱ፤ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት የዘረፉ ቡድኖች አንድ ቦታ መሽገው አገሪቱን የሁከት ማዕከል እያደረጓት ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሁከት በማስነሳት ዜጎች በለውጡ ላይ እምነት እንዳይኖረው ጥረት የሚያደርጉ ቡድኖች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የተለያየ እምነትና አመለካከት ያላቸው የ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጥያቄ በአንድ ጀምበር የሚመልስ ኃይል ስለማይኖር ለዚህም ትዕግሥት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ከኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ በሰላም መፈታት ጀምሮ በርካታ አገራዊና ቀጠናዊ ለውጦች መካሄዳቸውን አቶ ወንድሙ ገልጸዋል።

"ዛሬ ትናንት አይደለም" የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ በለውጡ የተገፉ ቡድኖች የሚፈጥሩት ችግር እንጂ፤ መንግሥት በዜጎች ላይ የሚያደርሰው በደል የለም ብለዋል።

አገሮች የበለጸገ ኢኮኖሚና የዳበረ ዴሞክራሲ የገነቡት ተባብረውና ተግባብተው በመሥራታቸው መሆኑን አቶ ወንድሙ አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያም ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ገዥው ፓርቲ፤ መንግሥት፤ ልሂቃን፤ የሲቪክ ማኅበራት ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በሚያጎሉ ጉዳዮች ላይ መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን የፖሊሲ ሰነድ ቀርጸው ለሕዝብ ከማሳወቅ ይልቅ፤ የሌሎችን እንከን በመፈለግ ትኩረት እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ ወንድሙ፤ይልቁንም ፓርቲዎቹ ሕዝቡን የሚያሻግር አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም