ቀጥታ፡

ግብጽ ከአስዋን ግድብ የምታባክነው ውሃ የህዳሴ ግድብን በተያዘለት ጊዜ መሙላት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14/2012(ኢዜአ) ግብጽ ከአስዋን ግድብ በትነት የምታባክነው ውሃ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውሃ መሙላት የሚያስችል መሆኑን የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራአስኪያጅ ገለጹ።

የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራአስኪያጅና የድርድሩ ተሳታፊ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ በግድቡ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የምትገነባው ህዝቦቿን ከድህነትና ከጨለማ ለማውጣት መሆኑ ለማንም ግልጽ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ በራሷ የተፈጥሮ ሃብት፣ በራሷ ጉልበትና በራሷ ገንዘብ በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሆኖም ለአባይ ወንዝ ምንም አስተዋጽኦ የሌላት ነገር ግን የወንዙ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ግብጽ በግድቡ ላይ መርህ የሌለው ተቃውሞ እያሰማች መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለአባይ ወንዝ 86 በመቶን የምታበረክት ብትሆንም በጋራ የመጠቀምን መርህ ተከትላ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ለውሃ ሙሌት በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች።

የወንዙ እልፍ አመታት ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ግብፅ ግን በየዓመቱ ከአስዋን ግድብ በትነት የሚባክነውን ያክል ውሃ እንኳን ኢትዮጵያ ልትይዝ አይገባም "ባልበላውም ጭሬ ላፍስሰው" የሚል ግትር አቋም ይዛለች ብለዋል።

 አቶ ፈቅ እንዳሉት ኢትዮጵያ በተፈጥሯ ሃብቷ የመልማት መብቷን ማንም ሊሰጣት ማንም ደግሞ ሊከለክላት አይችልም።

በመሆኑም በመጪው ሃምሌ ወር በእቅዷ መሰረት ግድቡን ውሃ በመሙላት በተግባር ማሳየት አለባት ብለዋል።

ኢትዮጵ ይህን ስታደርግ የግብጽም ይሁን ሱዳን የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ የሚያደርጉት ጥረት መቋጫ ያገኛል ነው ያሉት።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌር ዶክተር ሰዒድ አህመድ እንደሚሉት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶች ንትርክ አያጣቸውም።

ቱርክ በኤፍራጠስና ጢግረስ ወንዝ ላይ ግድብ መስራት ስትጀምር የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ሶሪያና ኢራቅ ግድቡን ለማስቆም ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁንና ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር አገሮቹ ተቃውሟቸውን ትተው ቱርክም የልማቱ ተጠቃሚ ሆና መቀጠሏን አስረድተዋል።

የግብጽም አሁናዊ ንትርክ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ መሙላት ሲጀምር መቋጫ የሚያገኝ ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉት ድርድር የቴክኒክ ጉዳይ ቢሆንም ግብጽ ግን የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አቅርባለች።

ይሁንና ኢትዮጵያ እስከመጨረሻው ለድርድር በሯን ክፍት ማድረግና ከድርድሩ ጎል ለጎንም የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ መጠቀል አለበት ብለዋል አቶ ፈቅ።

ግብጾች በአባይ ውሃ ላይ ምንም አይነት አስተዋፅኦ ሳይኖራቸው "ብቸኛ የታሪክ ባለቤት ነን፤ ኢትዮጵያ ልትጠቀም አይገባም" የሚል አቋም መያዛቸው በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም።

እኤአ በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ውልም ሆነ በ1959 በግብጽና ሱዳን መካከል የአባይን ውሃ ለመከፋፈል የተፈረመውን ውል ኢትዮጵያ ወድቅ አድርጋዋለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ የሚያስችለው የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ቀደም ሲል ለተፈራረሟቸው ስምምነቶች ኢትዮጵያ ዕውቅና እንድትሰጥ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በኩል ግን የአገራቱ ፍላጎት እንደቀደመው ሁሉ ውድቅ የተደረገ ሲሆን ግድቡን በማጠናቀቅ ህዝቦቿን ከጨለማ ለማላቀቅ የያዘችውን እቅድ ለማሳካት ዝግጁ ሆናለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም