በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ህክምና ማዕከል ተቋቋሞ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ህክምና ማዕከል ተቋቋሞ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
መተማ ሰኔ 13/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የመተማ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ህክምና ማዕከል ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ እንደገለፁት የኮሮና ህክምና ማዕከሉ ሰማንያ የተኝቶ ማከሚያ አልጋዎች ያለው ነው።
የተቋቋመው የህክምና ማዕከል ለሴቶች፣ ለወንዶችና ለህፃናት የተለያየ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ታማሚዎችን በአግባቡ ለይቶ በማከም በፍጥነት እንዲያገግሙ ለማድረግ የተመቻቸ መሆኑን ገልፀዋል ።
ይሁን እንጂ የህክምና ማዕከሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሜካኒካል ቬንትሌተር እጥረት ያለበት በመሆኑ የፅኑ ህሙማን ታካሚዎች ካጋጠመው ለጊዜው አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን ተናግረዋል ።
ለህክምና ባለሙያዎችና ለታካሚዎች የሚሆን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁስ የተሟላ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም እጥረት እንዳይገጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
የመተማ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሰጠኝ ነጋሽ በበኩላቸው የኮሮና ህክምና አገልግሎትን መጀመር የሚያስችል ግብዓትና ባለሙያ ተሟልቷል።
ለህክምና ባለሙያዎችና ለታካሚዎች የምግብ አገልግሎት የሚሰጥና የሚያቀርብ የምግብ አቅራቢ ኮሚቴ መዋቀሩንም አስረድተዋል፡፡