ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአፍሪካ ቀንድ ተምሳሌት ነው - አምባሳደር ዳይሱኬ ማቱሱንጋ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ተምሳሌት መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማቱሱንጋ ተናገሩ።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው አረንጓዴ ልማት በተለይም ከፊል ደረቃማ ለሆነው የምስራቅ አፍሪካ አየር ንብረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው አረንጓዴ ልማት ከድህነት ለመውጣትና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከፍተኛ ሚና አለው'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አገራቸው ጃፓን ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።

ጃፓን በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የደን ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ የአገራቸው መሬት ሁለት ሶስተኛው በደን የተሸፈነ ነው።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ጃፓን ጠንካራ የደን ፖሊሲን በማውጣት ተግባራዊ በማድረጓ እንደሆነ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት አራት ቢሊዮን ችግች ለመትከል እቅድ ይዛ ማሳካቷ ይታወሳል።

በተለይም ሃምሌ ወር በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን ብቻ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አለምን አስደምማለች።

በተያዘው ዓመትን አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየተከናወነ ነው።

አገሪቷ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም በአገር አቀፍ ደረጃ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ይዛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም