ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የመንገድና የእግረኛ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች አስመረቀ

አዲስ አበባ ሐምሌ1/2010 የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶችና አዲስ የእግረኛ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስመርቋል። በዛሬው ዕለት ከተመረቁት መንገዶች ከገርጂ መብራት ኃይል እስከ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአውጉስታ-ቤቴል-ዓለም ባንክ እና ሌሎችም ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አንድ የእግረኛ ማሻሻያ ፕሮጀክት በዛሬው እለት ተመርቀዋል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል ስድስቱ ባለስልጣኑ በራስ ሃይል የገነባቸው ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ በሁለት ስራ ተቋራጮች የተገነቡ ናቸው። የእግረኛ መንገዶቹን ለተጠቃሚዎች ምቹ የማድረግ ስራ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ በተደራጁ 26 ማህበራት አማካኝነት ነው ያከናወነው። የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ባለስልጣኑ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ 110 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በራስ ሃይልና በስራ ተቋራጮች እያከናወነ ነው። በዛሬው እለት የተመረቁት ዘጠኝ መንገዶች በአጠቃላይ 12 ኪሎሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ ሲሆኑ፤ ለግንባታቸው ደግሞ 550 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ነው የተናገሩት። የእግረኛ መንገዱ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ሲሆን በ101 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መገንባቱንም ነው ያስረዱት። ከ70 በመቶ በላይ እግረኛ ባለባት በአዲስ አበባ ከተማ የእግረኛ መንገዶች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አካል ነውም ብለዋል። በ2011 በጀት ዓመት 70 ኪሎ ሜትር ላይ የእግረኛ መንገድ ማሻሻያው እንደሚቀጥልም ነው ያብራሩት። መንገድ የአንድ ከተማ የትራንስፖርት የደም ስር ከመሆን ባሻገር የስልጣኔና የውበት መገለጫም ነው ያሉት ኢንጂነር ሃብታሙ ህብረተሰቡ በርካታ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸውን መንገዶች ደህንነት መጠበቅ ይገባዋልም ብለዋል። የከተማዋ ከንቲባ ዲሪባ ኩማ በበኩላቸው የመንገድ ግንባታ ለሀገርና ከተማ እድገት መፋጠን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልፀዋል። ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ከ 4 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት የሚሸፍኑ መንገዶች ማስገንባቱንም ጠቅሰዋል። በዚህም አጠቃላይ የከተማዋ የመንገድ ሽፋን 23 በመቶ ማድረስ መቻሉን ነው የገለፁት። የልማቱ ባለቤት የሆነው ኀብረተሰብ ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መንገዶች የሁሉም የጋራ ሀብቶች መሆናቸውን ተገንዝበው ለመንገዶቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግም አሳስበዋል። በምረቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎችም የመሰረተ ልማቶቹ ግንባታ ለሀገር ልማት ዋልታ መሆኑን ገልፀው ኀብረተሰቡ መንገዱ የእኔ ነው ብሎ እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም