ቀጥታ፡

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫ ከተሳሳተ አመላካከት የተነሳና አድሏዊ ነው... የታሪክ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ከተሳሳተ አመላካከት የተነሳና አድሏዊነት የታየበት ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሑራን አስታወቁ።

ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እያሳየች ያለው አቋምም መሬት የረገጠ አይደለም ብለዋል።

በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ስር የሚገኘው ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ሳይደረስ የውሃ ሙሌት መጀመር የለባትም የሚል መልዕክት በትዊተር ገጹ አስተላልፏል።

በምስራቅ አፍሪካ የሚገኘው 257 ሚሊዮን ሕዝብ የኢትዮጵያን ጠንካራ አመራርነት ይፈልጋል፤ ይህም ማለት አገሪቷ ፍትሀዊ ስምምነት ላይ መድረስ አለባት ብሏል።

ኢዜአ በምክር ቤቱ መግለጫና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እያሳየች ያለውን አቋም አስመልክቶ የታሪክ ምሑራንን አነጋግሯል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ አህመድ መግለጫው የአሜሪካን መንግስት አቋም ይወክላል ብለው እንደማያምኑ ገልጸው የተነሳው ሀሳብ ከተሳሳተ አመለካከት የመነጨ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን የግድቡን ውሃ ከመሙላት የሚያቆማት ኃይል እንደሌለና ይህንን አቋሟን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ማስረዳት እንደሚጠበቅባትም ተናግረዋል።

ከሱዳን ጋር በተያያዘም አገሪቷ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እያሳየች ያለው አቋም በተወሰነ ደረጃ የመለዋወጥ ሁኔታ እንዳለውና የግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

የሱዳን ቋሚ ያልሆነ አቋም ከውጫዊ አካላት የሚደርስባት ተጽዕኖና ጫና የመጣ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው ለሱዳን አዋጪ የሚሆነው በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከምታምነው ኢትዮጵያ ጎን መቆም ነው ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኪተቦ አብዲዮ በበኩላቸው የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫ በአንድ ጉዳይ ላይ ያላትን የተሳሳተ ድርብ አመለካከት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2012 በሱዳን መዲና ካርቱም የተፈረመውን የመርሆዎች ስምምነት መሰረት አድርጋ የግድቡን የውሃ ሙሌት ማድረግ እንደምትችልም ተናግረዋል።

ከቴክኒካዊና ከአየር ንብረት ሁኔታው አንጻር ኢትዮጵያ የውሃውን ሙሌት ማድረግ አስገዳጅ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ካላት አቋም ጋር በተያያዘ ግራ የመጋባት ሁኔታ እንደሚታይባትና የግድቡ ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ አቋም ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ሰፊና ረጅም ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሕዝባዊ ትስስር አላቸው ያሉት ዶክተር ኪተቦ ለሁለቱ አገራት በጋራ ከማደግና ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም 74 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም