በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

ሚዛን ፣ሰኔ 13 /2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

የሚዛን አማን ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ ረዳት ኢንስፔክተር ይቅደም አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ዛሬ ከጠዋቱ 1 ሰዓት አካባቢ ላይ ነው ።

ከሚዛን አማን ወደ ሸዋ ቤንች ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ3 ደህ 12895 የሆነ የሕዝብ ማመላለሻ አይሱዙ ከሰሜን ቤንች ወደ ሚዛን አማን ከሚጓዝ ኮድ 1 ደህ 23301 ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ጋር በመጋጨቱ ነው።

አደጋው የደረሰው ሚዛን አማን ከተማ ልዩ ቦታው መድሀኒተዓለም አካባቢ ሲሆን አንድ እግረኛን ጨምሮ የባጃጅ አሽከርካሪውና በባጃጅ ውስጥ የነበሩ አንዲት ሴት ሕይወታቸው ወዲያውኑ ማለፉንም ረዳት ኢንስፔክተር ይቅደም ተናግረዋል።

በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን ተጎጂዎች በሚዛን ቴፒ ቲቺንግ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

የአደጋው መንስኤ የሕዝብ  ማመላለሻ አይሱዙው መስመሩን ሳይጠብቅ በመጓዙ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም