ቀጥታ፡

የግብጽ "አቋሜን አለቅም" ማለት የሶስቱ ሀገራት ድርድር በውጤት እንዳይታጀብ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2012(ኢዜአ) ግብጽ ከመሰረታዊ ፍላጎቷ ይልቅ "አቋሜን አለቅም" ማለቷ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ እየተካሄደ ያለው ድርድር ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉ ተገለጸ። 

የግብጽ ከሶስተኛ ወገን መፍትሄ የመሻት እምነት ከንቱ ልፋት ነውም ተብሏል።

አንድ ሀገር በሉዓላዊ ግዛቱ የሚገኝን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም የመልማት መብት እንዳለው ሁሉ ኢትዮጵያም 86 በመቶ ድርሻ ባላት የዓባይ ወንዝ የልማት ፍላጎቷን ለማሟላት የሕዳሴ ግድቧን ግንባታ ጀምራለች።

ሕዝቧን ከጨለማ ብሎም ከድህነት የማውጣት ራዕይ ሰንቃ መገንባት የጀመረችው የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 74 በመቶ መድረሱንም መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይ በታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና በመካከላቸው መተማመን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።

የምስራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅና የተደራዳሪ ቡድኑ አባል አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን መተማመን ለማጎልበት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አገራቱ በግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አለመሆናቸውንም በጥናት ጭምር በማስደገፍ ለማስረዳት ተሞክሯል ብለዋል።

"ግብጽም ሆነች ሱዳን በተቻላቸው አቅም የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ቢያስቆሙ ፍላጎታቸው ነው" ያሉት አቶ ፈቅ፤ ያ ሳይሆን ሲቀር "የግድቡን መጠንና የውሃ ሙሌት የማጓተት ሙከራ ማድረጋቸው የማይቀር ነው" ብለዋል።

በተለይ በግብጽ በኩል እየታየ ያለው ግድቡ ውሃ መያዝ እንዳይጀምር የማድረግ የመጨረሻ ሙከራ መሆኑን ነው አቶ ፈቅ የሚናገሩት።

አገራቱ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ድርድሮችን እያካሄዱ ቢሆንም በግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ምክንያት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለመቻላቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም ግብጽ ከመሰረታዊ ፍላጎቷ ውጪ ''አቋሜን አልለቅም'' ማለቷ ድርድሩን ውጤት አልባ እንዳደረገው ነው የተናገሩት።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን እያደረጉት ባለው ድርድር የጋራ መግባባት እንዳይደረስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ያሏቸውንም አብራርተዋል።

ግብጾች የሕዳሴው ግድብ ድርድር የቴክኒክ ጉዳይ መሆኑን ቢረዱም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አቅጣጫ እንዲይዝ እያደረጉ መሆኑንም ነው የገለጹት።

እንደ አቶ ፈቅ ገለጻ የትኛውም አካል በአንድ አገር ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ መግባት የማይችል በመሆኑ ሶስቱ አገራት በሰከነ መንፈስ መፍትሄ ከመፈለግ ውጭ አማራጭ የላቸውም።

ግብጾች አሁንም ቢሆን ባለችው ጊዜ ራሳቸውን አረጋግተውና አዘጋጅተው የሚያወሳስቡትን ጉዳይ በማቆም ወደ እውነታው መመለስ አለባቸው ነው ያሉት።

በአዲስ መልክ የተጀመረው የሶስቱ አገራት ድርድር መቋጫ ሳያገኝ ግብጽ ጉዳዮን በድጋሚ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ልካለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም