ቀጥታ፡

የነገውን ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ ለመመልከት ተገቢው ጥንቃቄ ይደረግ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በዘመናቸው የገጠማቸውን አስደማሚ የፀሃይ ግርዶሽ የተፈጥሮ ክስተት ሲመለከቱ ከጥንቃቄ ጋር እንዲሆን የዘርፉ ተመራማሪዎች መክረዋል።

ይህን መልካም አጋጣሚ በተገቢው ትኩረት ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን ተሰማ ለኢዜአ እንዳሉት ታሪካዊውን የተፈጥሮ ክስተት ለማየት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

የፀሃይ ግርዶሹን ለማየት ከተሰራ መነፅርና በቤት ውስጥ ከሚዘጋጁ መሳሪያዎች ውጪ መመልከት ለጉዳት ይዳርጋል ነው ያሉት።

ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ሰሎሞን ''ሁነቱን እንዳታዩ ቤት ተዘግቶባችሁ ቁጭ በሉ ማለት ሳይሆን ወጥታችሁ ስታዩ ጥንቃቄ አድርጉ ለማለት ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል ይህን በኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በኋላ የሚታየውን ቀለበታዊ ግርዶሽ ቀርፆና ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ ለመስራት ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል ዶክተር ሰሎሞን።

ይህን ሁነት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በቴሌቪዥን በቀጥታ እንዲከታተለው ይደረጋልም ብለዋል።

ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ የሚከሰተው መሬት፣ ጨረቃና ፀሐይ በሚያደርጉት መስተጋብር መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ። 

ፀሐይ፣ ምድርና ጨረቃ በሰልፍ ሲሰደሩ ግርዶሽ ይከሰታል።

ይህ ማለት ጨረቃ በፀሐይና በመሬት መሐል ድንገት ስትደነቀርና ፀሐይን እንዳናያት ስትጋርድብን ማለት ነው።

የነገው ቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽ ከኮንጎ ተነስቶ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ይከሰታል።

በኢትዮጵያም ዋናው ግርዶሽ ከምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ከወለጋ ተነስቶ ከፊል ጎጃም፣ ጎንደርና ወሎ በተለይም ላልይባላ ላይ ይከሰታል።

እነዚህና ሌሎችም አካባቢዎችን የሚያዳርስ ሲሆን ጎንደር ደብረታቦር፣ ወሎ አላማጣ፣ መቀሌ እንዲሁም አዲስ አበባና ሌሎች ስፍራዎች ለተወሰኑ ሰከንዶች ጨለማ እንደሚሆኑ ነው ዶክተር ሰሎሞን የገለፁት።

ወደ መካከለኛው ምስራቅ በመሻገርም የመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኦማንን ካካለለ በኋላ ወደ እስያ አገራት በመዝለቅ በደቡብ ፓኪስታን፣ በሰሜናዊ የሕንድ ግዛትና በቻይና በመከሰት ፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ እንደሚያበቃ ይጠበቃል።

ዶክተር ሰሎሞን ”ኢትዮጵያ ለግርዶሹ ተስማሚ የደመና፣ የሙቀት መጠንና ግርዶሹ በግልጽ የሚታይባት ስለመሆኑ የተደረገው ጥናት አመላክቷል” ብለዋል።

በተጨማሪም የግርዶሹ ከ86 እስከ 98 በመቶ የሚታይባት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ እንደሚያደርጋትም ተናግረዋል።

ግርዶሹ በአዲስ አበባም 86 በመቶ ይስተዋላል ነው ያሉት።

በተለይ በላልይበላ ከ98 በመቶ በላይ አካባቢው ጨለማ ስለሚሆንና የፀሃይ ግርዶሹ በሚገባ የሚታይ በመሆኑ ታሪካዊውን የጸሃይ ግርዶሽ ለማየት በስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች ተመራጭ አድርጎት ነበር።

ይሁንና ዓለምን ያጠቃው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደቡ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት አልቻሉም፤ አገሪቷም ከሁነቱ ታገኝ የነበረውን ጥቅም አጥታለች።

የግርዶሹ ክስተት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ6 ሠዓታት የሚቆይ ሲሆን በኢትዮጵያም ነገ ከማለዳው 12፡50 እስከ ቀኑ 6፡30 ቆይታ ይኖረዋል።

ቀለበታዊው ግርዶሽ ሶስት ሠዓታት የሚቆይ ሲሆን ዋናው ቀለበታዊው ግርዶሽ በላልይበላ ለ38 ሰከንድ የሚታይ ይሆናል፤ በዚህም ጊዜ አካባቢው ጨለማ ይሆናል።

ቀለበታዊው የፀሃይ ግርዶሽ ከ18 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የተከሰተ ሲሆን ሙሉ የፀሃይ ግርዶሽ ከ46 ዓመት በኋላ የሚከሰት መሆኑ ነው የሚነገረው።

ይህን ታሪካዊ ክስተት ለመመልከት ግን አዋቂዎችም ሆኑ ህጻናት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

ግርዶሹን ለመመልከት በተዘጋጀ መነፅር አልያም ቀላል ካርቶን ጥቁር ቀለም በመቀባትና ጨረር እንደማያስገባ በማረጋገጥ፣ ሰፋፊ አረንጓዴ የዛፍ ቅጠሎችን ከሰል በመቀባት እንዲሁም የፊልም ቁርጥራጮችን በመጠቀም መመልከት ይቻላል ተብሏል።

ያለ መከላከያ መጠቀምና በቪዲዮ መቅረፅ ዓይንን ለጉዳት ስለሚዳርግ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

እንደ ዶክተር ሰሎሞን ገለጻ በዕለቱ የሙቀት መጠን፣ የንፋስና የደመና እንቅስቃሴ ስለሚቀየር የአየር ሁኔታ ይዛባል፤ በተወሰነ መልኩም የኤሌክትሪክ ፍጆታ ይጨምራል።

ግርዶሹ በሚፈጠርበት ሠዓት የጨረቃ ትክክለኛ ቅርጽ፣ የመሬትና የፀሐይ ልኬት ጥናት የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ለጥናቶቻቸው በቂ መረጃ ያገኛሉ።

በነገው ዕለት በላልይባላ በሚካሄደው ስነ-ስርዓት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተመራማሪዎች እንዲሁም የክልሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንደሚገኙ ዶክተር ሰሎሞን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም