ቀጥታ፡

ጥበበኛ እናቶች የሚገባቸውን ክብር፤ጥበባቸውም የሚገባውን ዋጋ እንዲያገኝ ይሰራል - ኢ/ር ታከለ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የሸክላ ውጤቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና ለሙያተኞቹም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናገሩ።

ከተማ አስተዳደሩ "እንሥራ የሸክላ ማዕከል"ን በማቋቋም በሸክላ ስራ ለተሰማሩ አንድ ሺህ እናቶች ዛሬ አስረክቧል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ውስጥ የተቋቋመው ማዕከሉ ለተረከቡት አንድ ሺህ እናቶች የተሟላ የሸክላ ማምረቻ ቁሳቁስና የምርት መሸጫ ቦታ አለው።

የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በማዕከሉ ርክክብ ላይ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ የሸክላ ስራ ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው።

በአገሪቷ ለሸክላ ስራ ትኩረት እንዳልተሰጠ ጠቅሰው በሙያው የተሰማሩ ሰዎች የልፋታቸውን እንዲያገኙ በአገር ውስጥ፣ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ የገበያ ትስስር የመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

ከተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የሸክላ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ንግግር እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

'ሸክላ ሠራተኞች በጥበበኛ እጆቻቸው ውብ ነገር እየሰጡን ዘመናት ተቆጥረዋል በምላሹ ግን ያልተገባ ስም እንጂ ጠብ የሚል ጥቅም አላገኙም' ብለዋል።

በመሆኑም "ጥበበኛ እናቶቻችን የሚገባቸውን ክብር፤ ጥበባቸውም የሚገባውን ዋጋ እንዲያገኝ የምንሰራ ይሆናል" ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ክፍለ ከተማው በሸክላና ሸማ ስራ ታዋቂ ቢሆንም ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቁመው በቀጣይ በዘርፉ ለተሰማሩ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በክፍለ ከተማው ከ103 ሺህ በላይ ሕዝብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የእነዚህን ዜጎች ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ሙያተኞቹ በከፍተኛ ድካም የሚሰሩ ቢሆንም የሚያገኙት ክፍያ አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንስራ የሸክላ ማዕከልን የተረከቡት እናቶች በበኩላቸው የመስሪያና የመሸጫ ችግራቸው ስለተፈታላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩን አመስግነው በቀጣይም ምርቶቻቸውን በተለያዩ ባዛሮችና ለውጭ ገበያም ጭምር እንዲያቀርቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም